ልጆች፤ የሣይንስ ሙዚየምንእናስተዋውቃችሁ

You are currently viewing ልጆች፤ የሣይንስ ሙዚየምንእናስተዋውቃችሁ

ልጆች እንዴት ከረማችሁ? የክረምት የዕረፍት ጊዜያችሁን በጥሩ ሁኔታ እያሳለፋችሁ እንደሆነ እምነታችን ነው። በከተማችን አዲስ አበባ ለእናንተ ለልጆች በአይነታቸው ልዩ እና ዘመናዊ የሆኑ የተለያዩ የጊዜ ማሳለፊያዎች እንዳሉ ታውቃላችሁ? ልጆች በክረምቱ ጊዜ አይታችሁ እውቀት እንድትጨብጡ እና የአስተሳሰብ አድማሳችሁ እንዲሰፋ ማገዝ ከሚያስችሉ ቦታዎች አንዱ የሆነውን የኢትዮጵያ የሳይንስ ሙዚየምን እናስቃኛችሁ፡፡

የሣይንስ ሙዚየም በመሐል አዲስ አበባ ከተማ፣ በአራት ኪሎ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት እና አንድነት ፓርክ የሚገኙበት አካባቢ ነው የተገነባው፡፡ ሕንፃው በልዩ ቅርፅ የተገነባ፤ ከላይ ሲታይ ክብ እና የቀለበት ቅርጽ ያለው ነው፡፡ ሣይንስና ጥበብን አጣምሮ የያዘ ነው። 

ሕንጻው ክብ ቅርፅ መያዙ እና በጉልላት መልክ መሠራቱ፤ የሠው ልጅ በማያቋርጥ ሂደት ውስጥ ያለውን እድገትና ጥበብ የሚያመላክት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፤ ኢትዮጵያ በአስገራሚ ፍጥነት በማደግ ላይ ካለው ቴክኖሎጂ ጋር ለመጣመር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይም ነው፡፡

ሙዚየሙ በ6 ነጥብ 78 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ የሣይንስ እድገት ከፍተኛ አበርክቶ ይኖረዋል። የሙዚየሙ ውስጣዊ ክፍል 1 ሺህ 400 ሜትር ስኩየር ስፋት አለው፡፡ ድምፅ የማያስተላልፍ ቋሚ እና ጊዜያዊ የአውደ ርዕይ ቦታዎችም አሉት። ሙዚየሙ ሀገር በቀል እጽዋትና ውብ አበቦች የተሸፈነ፣ በቂ የመኪና ማቆሚያ ስፍራም ያለው ነው።

ልጆችዬ፤ “ይህ በአይነቱ ልዩና ዘመናዊ የሆነው የሣይንስ ሙዚየም ውስጡ ምን ምን እንዳለው ለማወቅ ያጓጓል አይደል?” አዎ፤ በዚህ ሙዚየም ብዙ ድንቅ ሣይንሳዊ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ወጤቶች አሉ፡፡ በቋሚነት የሚጎበኙ አምስት የኤግዚቢሽን ሥፍራዎችንም አካትቷል። የመጀመሪያው ክፍል፤ የሠው ሠራሽ አስተውሎትን የሚመለከት ነው፡፡ ይህ ክፍል ፈጠራ ለጤና፣ ለግብርና፣ ለስማርት ሲቲ፣ ለአገልግሎቶች (ለምሳሌ ለካፌና ለሆቴል) በሮቦቲክስ  እንዴት አገልግሎት መስጠት እንደሚችል የሚያሳይ ነው፡፡ ክፍሉ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ከየት ተጀምሮ የት እንደደረሰ እና ወዴት እንደሚሄድ በዝርዝር መረጃ ይሰጣል፡፡

ሁለተኛው ከባቢያዊ ክፍል በመባል ይጠራል፡፡ በዚህ ክፍል የሠው ልጅ በተፈጥሮ ህግ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ መኖር ሲገባው ኃላፊነቱን በሚገባ መወጣት ካልቻለና የተፈጥሮ ህግን ከሳተ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ የሚያሳይ ነው፡፡ የተፈጥሮ ህግ እንዳለ አምነንና አክብረን መኖር አንዳለብን የሚያስተምር ነው፡፡ የሠው ልጅ ተፈጥሮን በማጥፋት የሚደርስበትን ጉዳት እንዲሁም በማልማት እና መልሶ በመጠቀም ሂደት ውስጥ የሚያገኘውን ጠቀሜታ በጉልህ የሚያስረዳ ነው፡፡ 

በሙዚየሙ የሚገኘው ሦስተኛው ክፍል የግብርና ክፍል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ግብርናን በዓለም በቀዳሚነት ከጀመሩ ጥቂት አገራት አንዷ እንደሆነች፣ አሁንም የግብርናውን ዘርፍ በስፋት እየተጠቀመች እንደምትገኝ እንዲሁም ዘርፉን ለማሳደግ እየተሠራ ያለውን እና የነገውን ግብርና የዕድገት ደረጃ የሚያመላክት ክፍል ነው። እንደ ጤፍ፣ ቡና እና እንሰት የመሳሰሉ  በግብርናው መስክ ያሉ ጸጋዎቻችንን ለዓለም ያስተዋወቀች ሀገር መሆኗን የሚገልጽ መረጃ በዚሁ ክፍል ይገኛል፡፡ በተጨማሪም፤ ይህ ክፍል በአሁኑ ወቅት በትንሽ ውስን መሬት በዘመናዊ መንገድ እንዴት እርሻን ማሳደግ እንደሚቻል በስፋት የሚያስተምር ነው፡፡

አራተኛው  የውሃና ኢነርጂ ክፍል ነው፡፡ ከኬሚስትሪ፣ ከፊዚክስ እና ከሂሳብ ትምህርቶች ጋር የተያያዘ፣ በተግባር የተደገፈ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚያስችል ክፍል ነው፡፡

አምስተኛው የስፔስና የአየር ክፍል ነው፡፡ ይህም ከጠፈር ቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘ እና የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ቴክኖሎጂ ዕድገትን የሚያሳዩ መረጃዎች በስፋት ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም በሀገራችን የመጀመሪያ የሆነው ፕላኒቴሪየም (ዶም ሲኒማ) በሙዚየሙ ውስጥ ይገኛል። በሀገራችንም ሆነ በአፍሪካ በዓይነቱም ሆነ በቴክኖሎጂ ምጥቀቱ ልዩ የሆነው ይህ የሲኒማ ክፍል በክብ ቅርፅ የተሠራ እና ዘመናዊ የሆኑ የሣይንስ፣ የፈጠራ፣ የመሬት ተፈጥሮ፣ የሕዋ (ጠፈር) እና የምርምር ሃሳብ (ይዘት) ያላቸው ፊልሞች የሚታዩበት ነው፡፡

ልጆችዬ፤ በዚህ ጽሑፍ ስለ ሣይንስ ሙዚየም የተወሰነ መረጃ እንዳገኛችሁ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የእረፍት ጊዜያችሁን ተጠቅማችሁ ይህንን አስደማሚና አስደናቂ ሙዚየም እንድትጎበኙ እንጋብዛለን፡፡

በለይላ መሀመድ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review