በመዲናችን አዲስ አበባ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ መሰናዶዎች ይደረጋሉ፡፡ ባለፉት ቀናት ደግሞ የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች እና አዳዲስ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም በመዲናችን ከተሰናዱ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች መካከል የመጽሐፍ ውይይት፣ የሥዕል አውደ ርዕይ፣ የቴአትር መርሃ ግብር እና ሌሎች መሰናዶዎች ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡
መጻሕፍት
“የወዲያነሽ” የተሰኘው ልብወለድ መጽሐፍ ይመረቃል፡፡ ይህ የአንጋፋው ደራሲ የኃይለ መለኮት መዋዕል መጽሐፍ ከ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ የደራሲው አድናቂዎችና የጥበብ አፍቃሪያን በተገኙበት በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት (ወመዘክር ) አዳራሽ ነው ዛሬ በድጋሚ የሚመረቀው
በሌላኛው መረጃ፣ ዛሬ በደራሲና ተዋናይ ደመወዝ ጎሽሜ አዲሱ መጽሐፍ ላይ ውይይት ይካሄዳል፡፡ ከወር በፊት ለንባብ በበቃው “አዲሲቱ ኢየሩሳሌም” በተሰኘው መጽሐፍ ላይ ዛሬ ቅዳሜ ከ8:00 ሰዓት ጀምሮ ውይይት እንደሚደረግ ታውቋል፡፡ የውይይት መርሃ ግብሩ አዘጋጅና አቅራቢ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ሲሆን፣ ውይይቱን ያሰናዳው ደግሞ ዛጎል የመጻሕፍት ባንክ ነው፡፡ የውይይት መርሃ ግብሩ የሚካሄደው ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (FSS) አዳራሽ ውስጥ ነው፡፡ የመወያያ ስፍራ አድራሻው ደግሞ ቀበና፣ የካቶሊኮች ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት፣ ነጩ ሕንፃ አጠገብ፣ መቅድም ኢትዮጵያ ቢሮ ውስጥ ነው ተብሏል፡፡
የአንጋፋው ደራሲና ተርጓሚ ሳህለ ሥላሴ ብርሃነማርያም 90ኛ ዓመት የልደት በዓል ይከበራል፡፡ ሳሕለ ሥላሴ ትናንት አርብ ነሐሴ 02 ቀን 2017 ዓ.ም. 90ኛ ዓመታቸውን ይዘዋል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ ነገ እሁድ ከ8፡00 ሰዓት ጀምሮ በወ መዘክር አዳራሽ ልደታቸውን መነሻ በማድረግ የደራሲው ስራዎች ላይ ውይይት ይደረጋል፡፡ በመርሃ ግበሩ ላይ ታዋቂና አንጋፋ ደራስያን ስለ ደራሲ ሳህለ ሥላሴ ስራዎች ንግግር ያደርጋሉ፡፡
ደራሲ ሳህለ ሥላሴ ከጉርምስና ዕድሜ ጀምረው ያለፉት ሰባ ዓመታት በርካታ ድርሰቶችን በመድረስና በመተርጎም ዘመን አይሽሬ የጥበብ ስራዎችን አበርክተዋል። ከሌሎች የሃገራችን ደራስያን በተለየ በሶስት ቋንቋዎች ድርሰቶችን ጽፈው ለንባብ አብቅተዋል። በአማርኛ፣ በጉራጊኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ነው ድርሰቶችን ለንባብ ያበቁት፡፡ ለአብነትም ሽኩቻና ባሻ ቅጣው በአማርኛ፤ The Afersata (ስለጉራጌ ባሕል)፣ Warrior King (ስለአጼ ቴዎድሮስ ጀግንነት) በእንግሊዝኛ፤ የሻንጋ ቃያ (በጉራጊኛ) ካሳተሟቸው በርካታ ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው። ሌላው ደግሞ በተርጓሚነት ደራሲው አንቱታን ያተረፉበት ሙያ ነው። በተለይ በፈረንሳይኛና በእንግሊዝኛ የተጻፉ በርካታ ድርሰቶችን ተርጉመዋል፡፡ ለአብነትም የሁለት ከተሞች ወግ፣ እምዩ፣ የሃገር ልጅ፣ መከረኞቹ ተጠቃሽ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ በርካታ የመጽሐፍ ዳሰሳዎችና ሂሶችን በቀድሞ ጋዜጦችና መጽሔቶች በማስነበብም ይታወቃሉ፡፡ የጥበብ አፍቃሪያንም የአንጋፋው ደራሲ ሳህለ ሥላሴ ልደትን መነሻ በማድረግ በሚደረገው በዚህ የጥበብ መርሃ ግብር ላይ እንድትሳተፉ ተጋብዛችኋል፡፡
ሕይወትን ሙሉ በወደዱት መንገድ ሲመላለሱ እንደመኖር ያለ በረከት ከቶ የት ይኖራል?! እዚያም እዚህም ሳይረግጡ መኖር … የረጋ የሕይወት ጎዳና! በመጽሐፍ ዓለም መቅዘፍ – ደራሲና ተርጓሚ ሳህለሥላሴ ብርሃነማርያም!
“ጣፋጭ ፍልስፍና” የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ በረዳት ፕሮፌሰር ዋለልኝ እምሩ የተጻፈው አዲሱ መጽሐፍ ፍልስፍናዊ ጉዳዮችን በዝርዝር የተዳሰሰበት ነው ተብሏል፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም የሞራል ፍልስፍና፣ በፍልስፍና መደመም፣ ፍሬሽ ማን ሎጂክ እና ሌሎችም መጻሕፍት ለንባብ አብቅቷል፡፡ አሁን ደሞ ጣፋጭ ፍልስፍና የሚል አዲስ መጽሐፍ በያዝነው ሳምንት ለአንባብያን አድርሷል፡፡ መጽሐፉ በተለያዩ የመጽሐፍ መደብሮች ውስጥ ይገኛል ተብሏል፡፡
ሥዕል
የቡድን የግራፊክስ ጥበብ አውደ ርዕይ በመታየት ላይ ነው፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት ረዕቡ ሐምሌ 30 ቀን፣ 2017 ዓ.ም በይፋ የተከፈተው የጥበብ አውደ ርዕይ የተለያዩ ሰዓሊያን ስራዎች በመታየት ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ የጥበብ አውደ ርዕይ ሥራዎቻቸውን ካቀረቡ ከያኒያን መካከል ታደሰ ባይሳ፣ ሚኪያስ ሰለሞን፣ ቤርሳቤህ አለማየሁ፣ ምህረት እሸቱ፣ ዳግማዊ ጸጋዬ፣ ሱራፌል መክብብና የሌሎችም ከያኒያን የጥበብ ሥራዎች የቀረበቡበት አውደ ርዕይ ነው። አውደ ርዕዩ እስከ ፊታችን ነሃሴ 28 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ድረስ ይቆያል፡፡ የጥበብ ዓውደ ርዕዩ እየታየ ያለው ደግሞ በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል ውስጥ በሚገኘው የፈንደቃ የባህል ማዕከል ውስጥ ነው፡
በአብርሃም ገብሬ