የይዞታ ካርታ አዘጋጃለሁ በሚል ከአንድ ግለሰብ 50ሺህ ብር ጉቦ የተቀበለን የይዞታ ማረጋገጥና ምዝገባ ባለሙያ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
የወንጀል ድርጊቱ የተፈጸመው ሐምሌ 30 ቀን 2017 ዓ/ም ከቀኑ 5:00 ሠዓት በኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው ቤተል አካባቢ መሆኑን ፖሊስ አስታዉቋል።
ተከሳሽ ሳምሶን ፍስሀ በክ/ከተማው የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽ/ቤት የይዞታ ማረጋገጥና ምዝገባ ባለሙያ ሲሆን የግል ተበዳይ የሆኑት አቶ ባይሳ ሚልኬሳ በፍርድ ቤት በነበራቸው የፍትሐብሔር ክርክር ጉዳይ በማሸነፋቸውና ሲከራከሩበት የነበረው መሬት 397.58 ካሬ የይዞታ ካርታ እንዲዘጋጅላቸው በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ተሠጥቷል።
ግለሰቡም የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ይዘው ወደ ጽ/ቤቱ ባለሙያ በመቅረብ ካርታው እንዲሠራላቸው ቢያደርጉም ባለሙያው ግን የይዞታ ካርታውን 342 ካሬ አድርጎ በመስራቱ ፍርድ ቤቱ እንዲሰራ ያዘዘው 397.58 ካሬ ባለመሠራቱ ተስተካክሎ እንዲሠራ ተለዋጭ ትዕዛዝም ይሠጣል።
የግል ተበዳይ ይህንን ተለዋጭ ትዕዛዝ በመያዝ ወደ ጽ/ቤቱ ሲመለሱ በተከሳሽ በኩል ካርታውን ለማስተካከል 50ሺህ ብር እንዲከፍሉ በመጠየቃቸው ለፖሊስ በሠጡት ጥቆማ ገንዘቡን ሲቀበል እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ስር ሊውል መቻሉን ፖሊስ ገልጿል።
ፖሊስ በተጠርጣሪው ላይ ተገቢውን የምርመራ ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በላከዉ መረጃ አስታዉቋል።