ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ስኬት እየተሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ ገለጹ።
በሰላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት ከሁሉም ክልሎች እና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የሰላምና ጸጥታ ዘርፍ አመራሮች የምክክር መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።
ምክክሩ “ሰላማችንን ማጽናት ለኢትዮጵያ ማንሠራራት” በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ይገኛል።
በሀገራዊ የሰላም ግንባታ፣ የግጭት አፈታትና ሀገር ግንባታ ዙሪያ የተሟላ ግንዛቤ በመያዝ ልማትን ለማጎልበት የሚያስችል ግልጽነትና ዝግጁነት ያለው አመራር መገንባት የመድረኩ ዓላማ መሆኑ ተጠቁሟል።

የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት መንግስት ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም የፖለቲካ ምህዳርን ከማስፋት ጀምሮ የሰላም በሩን ክፍት በማድረግ በርካታ የታጠቁ አካላት ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጡ ማስቻሉን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የመንግሥት የሰላም ጥሪ እና የህግ ማስከበር ሥራዎች ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ለሀገር ልማት ማንሰራራት ትልቅ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
በቀጣይም ሰላም ሚኒስቴር የዘላቂ ሰላም እና የተቋማት ግንባታ ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
በመድረኩ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ካይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታን ጨምሮ ሌሎች የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።