በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በአዋሽ ወንዝ ሙላት ምክንያት የተጎዱ ዜጎችን የመደገፉ ተግባር ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።
የአዋሽ ወንዝ ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የሰበታ ሀዋስ፣ ዳዋ እና ኢሉ ወረዳዎች እንዲሁም በምዕራብ ሸዋ ዞን ደግሞ የኤጀሬ፣ ወልመራ እና ኤጀርሳ ለፎ ወረዳዎች ላይ ጉዳት አድርሷል።
የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ስንታየሁ ለገሰ እንዳሉት የወንዙ ሙላት ምክንያት በዞኑ ሰበታ ሀዋስ፣ ዳዋ እና ኢሉ ወረዳዎች በርካታ ዜጎችን ለጉዳት ዳርጓል።
ጉዳቱ ከደረሰ ቀን ጀምሮ በኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ እና ለሎች አካላትን በማስተባበር የዜጎችን ህይወት ለማትረፍና እና ንብረት ለማዳን በርብርብ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
በተደረገው እንቅስቃሴ በእነዚህ ወረዳዎች በውኃ ተከበው የነበሩ 22 ሺህ የሚጠጉ ዜጎችን በማውጣት ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።
በጉዳቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች የከፋ ችግር እንዳይገጥማቸው መጠለያ፣ ንጹህ መጠጥ ውሃ እና ምግብ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ስንታየሁ፣ ጉዳቱ ከፍተኛ በመሆኑ ከክልሉና ከፌዴራል መንግስት ጋር በቅርበት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በስፋራው ተገኝተው ድጋፍ ካደረጉ ባለድርሻ አካላት መካከል በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምዕራብ ሪጅን የአምቦ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ባይሳ ቦሶና፣ የዲስትሪክቱ ሠራተኞች ከወር ደመወዛቸው በማዋጣት ለተጎጂዎች ድጋፍ አርገዋል ብለዋል።
በዚህም 220 ሰዎችን ምሳ ከማብላት በተጨማሪ የዱቄት እና ሌሎች የእለት ደራሽ ድጋፍ መደረጉን ገልጸው ድጋፉ በብር ሲተመን 700 ሺህ ብር ግምት እንዳለውም አመልክተዋል።
የጉዳቱ ሰለባዎች በበኩላቸው የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ በመፍሰሱ በመኖሪያ ቤታቸውና የእርሻ መሬታቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።
ከተጎጂዎች መካከል አቶ ዳመነ ቀነኒ እንዳሉት፤ ወንዙ ከዚህ በፊት ጉዳት ቢያደርስም የአሁኑን ያህል ጉዳቱ በርትቶ አያውቅም።
ህብረተሰቡና የአካባቢው አስተዳደር ተባብረው በመስራታቸው በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ባይደርስም በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅትም በተጠለሉበት ስፍራ ድጋፍ እያገኙ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አቶ ቀነኒሳ ደጋጋ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው በጉዳቱ ንብረት መውደሙን ገልጸው በአሁኑ ወቅት እየተደረገላቸው ላለው የእለት ደራሽ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በአዋሽ ወንዝ ሙላት ምክንያት ዘንድሮ የደረሰው ጉዳት የከፋ መሆኑን ጠቁመው፣ መንግስትን ጨምሮ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ድጋፉን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።