የኮሪደር ልማቱ ለንግድ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው የዘርፉ ተዋንያን ገለፁ

You are currently viewing የኮሪደር ልማቱ ለንግድ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው የዘርፉ ተዋንያን ገለፁ

AMN – ነሐሴ 3/2017 ዓ.ም

የኮሪደር ልማቱ ለንግድ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው የዘርፉ ተዋንያን ገለፁ።

ሰሞኑን በተመረቀው የእንጦጦ አራት ኪሎ ፕላዛ ኮሪደር ላይ በሚገኘው ሜጋ ማተሚያ መፅሃፍት መደብር የሽያጭ ባለሞያ የሆኑት አቶ ግደይ ኪሮስ ለ ኤ ኤም ኤን እንደተናገሩት ኮሪደሩ ለንግድ ሱቆች ጥሩ እይታን ያጎናፀፈ በመሆኑ ደንበኞችን እየሳበላቸው ነው።

አቶ ግደይ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ የንግድ ቦታ አግኝተናል ያሉ ሲሆን፣ ህብረተሰቡ ከእለታዊ ፍላጎቱ አሻግሮ ማየትና ከለውጡ ጋር መላመድ እንዳለበት ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

በአካባቢው የኦፕቲክስ የሽያጭ ባለሙያ የሆኑት ወ/ሮ እናት ላቀው የንግድ ሱቁ ከልማቱ በፊት የነበረበት አካባቢ መልሶ ስለተሰጣቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው፣ ከበፊቱ በተለየ ለእይታ ማራኪ እና ምቹ ከመሆኑም በላይ መዝናኛ ስፍራ በአቅራቢያቸው መኖሩ አዳዲስ ደንበኞችን እንዲያፈሩ እንዳገዛቸዉ ተናግረዋል።

በአራት ኪሎ ፕላዛ የሂማ ካፌ ማናጀር አቶ ተመስገን ከተማ በበኩላቸዉ ዘመናዊ የሆነ የስራ ቦታ ማግኘት በመቻላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ኮሪደሩ የመኪና ማቆሚያ ስፍራን ታሳቢ አድርጎ መሰራቱ ለተጠቃሚም ሆነ ለንግዱ ማህበረሰብ ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረ ገልጸዋል።

በአራት ኪሎ ፕላዛ ውስጥ የጫማ ንግድ የምትሰራው ወጣት መስቀሌ ፍቃዱ በበኩሏ እጅግ የተዋበው ፕላዛ ለራሷም ሆነ ለደንበኞቿ ምቹ የሥራ ሁኔታ ፈጥሯል ትላለች፡፡

ቀደም ሲል የነበረችበት የሥራ ከባቢ ከአሁኑ ጋር በፍፁም የሚስተያይ አይደለም ያለችን ወጣቷ፣ የኮሪደር ልማት ሥራው ከተማዋን ከማዘመንም በላይ በንግዱ ዘርፍ ላይ ከፍተኛ የሆነ መነቃቃት እየፈጠረ መምጣቱን ገልፃለች፡፡

በተዋበው ፕለዛ ውስጥ በመሥራቴ ደስተኛም፤ ዕድለኛም ነኝ ብላለች፡፡

በሊያት ካሳሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review