የሕዳሴ ዘመን ትውልዶች

You are currently viewing የሕዳሴ ዘመን ትውልዶች

AMN – ነሀሴ 4/2017 ዓ.ም

ኢትዮጰያ “የአፍሪካ የውሀ ማማ” የሚል ስያሜ እንድታገኝ ምክንያት ከሆኗት ወንዞች መካከል አንዱ የታላቁ የአባይ ወንዝ መነሻ መሆንዋ እንደሆነ ይጠቀሳል፡

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ የውሃ ማማ የሚል ስያሜ ቢሰጣትም በወንዝ ፀጋዎቿ ብዙም ሳትጠቀምባቸው በርካታ ዘመናትን አሳልፋለች፡፡

ከዘመናት በፊት የኢትዮጵያን ዜጎች ከድህነት እና ከጨለማ ለማውጣት በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ መገንባት እንደሚገባ ታስቦ እንደነበር ታሪክ ያስረዳናል።

ሆኖም ግን ይህን እቅድ ወደ ተግባር ለመቀየር በርካታ ፈተናዎችና ተቃወሞዎች ገጥመውት ለዘመናት ሳይተገበር ቆይቷል፡፡

አሁን ላይ ጊዜው ፈቅዶና ደርሶ የታሰበውን እሳቤ እውን የሚያደርግ በአባይ ወንዝ ላይም ግድብ መገንባት የሚችል የሕዳሴ ዘመን ትውልድ ተፈጠረ፡፡

በወረሃ መጋቢት 2003 ዓ.ም በአባይ ወንዝ ላይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የግባታ የመሰረት ድንጋይ ተጣለ፡፡

ኢትዮጵያም እጅግ ተደሰተች፤ ልጆቿም ከዳር ዳር ደስታቸውን በተለያዩ መንገዶች ገለጹ፡፡

“ድር ቢያብር ነውና ተረቱ”፣ ሁሉም ከደቂቅ እስከ ሊቅ፣ ከድሃ እስከ ሀብታም ግድቡን በራሳችን አቅም እንገነባዋለን የሚል መፈከር አንግበው በይቻላል መንፈስ በአንድነት ተነሱ፡፡

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታም በኢትዮጵያዊያን አቅም ተገንብቶ አሁን ላይ ለውጤት በቅቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአስራ አንድ ወራት በፊት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከሚገኝበት ጉባ ላይ ተገኝተው ይህን የሚያጠናክር ንግግር አድረገዋል፡፡

“ከድሀነት አረንቋ አትወጡም፣ ግድቡንም በራሳችሁ አቅም መገንባት አትችሉም፣ ብልፅግናን እውን ማድረግ አይቻላችሁም ብለው ለተሳለቁብን ሁሉ አቅማችንን እና አንድነታችንን አስተባብረን የታለቁን የህዳሴ ግድብ ገንብተን በግልጽ ለማሳየት ችለናል።” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግድቡን ግንባታ ፍፃሜ እውን መሆኑን አሳውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) የታላቁን የህዳሴ ግድብ በወርሀ መስከርም እንደሚያስመርቁ መናገራቸውን ተከትሎ አዲስ ሚድያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያም በግድቡ መጠናቀቅ ዙሪያ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሰማቸውን ደስታ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል።

ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከመሰረቱ ጀምሮ በአቅማቸው ማዋጣታቸውን የተናሩት አንድ አባት መስከረም ወር ላይ ስለሚመረቅ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጰያዊያን ሃውልት ነው የሚሉት እኒህ አባት፣ ለልጆቻችን ጥቅም ያለው ከመሆኑ ባሻገር አንድ መሆን የቻልበት ነው ሲሉም ይገልጻሉ።

ግድቡን በጋራ ገንብተን ማጠናቀቃችን አንድነታችንን ያሳየንበት እንደሆነ እና በጋራ ስንቆም መፈጸም የማንችለው ነገር እንደሌለ ያሳየንበት ነው ብለዋል።

የትኛውም ስራ በጋራ ሲሰራ ዋጋው ላቅ ያለ እና የገዘፈ እንደሆነ የታላቁ ግድብ ግንባታ ትብብርና ውጤት ማሳያ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

እኒህ አባት የህዳሴ ግድቡ ግንባታ በስኬት እንዲጠናቀቅ ከገንዘባቸው በተጨማሪ በፀሎታቸውም መትጋታቸውን አስረድተዋል።

የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያን ከእለት ጉርሳቸው ሳይሰስቱ ያካፈሉበት እንደሆነ የገለፀው ሌላኛው ወጣት ደግሞ፣ ለእዚህ ደረጃ በቅቶ በማየቴ ደስታየ ወደር የለውም በማለት ተናግሯል።

የህዳሴ ግድብ መሰረት ሲጣል የመንግስት ሰራተኛ እንደነበሩ የሚያስታውሱት አቶ አጥናፉ ካሳ በበኩላቸው፣ከሚያገኙት ወርሀዊ ደሞዝ ለግድቡ ግንባታ ማዋጣታቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያዊያን ከአባቶቻችን ጀምሮ በጀግንነት እንታወቃለን ያሉት አቶ አጥናፉ፣ ችግሮችና ውጣውረዶች ሳይበግሩን ግድቡን ለፍፃሜ በማብቃታችን ትልቅ ደስታ ይሰማኛል ብለዋል።

ግድቡ እዳይጠናቀቅ የሚፈልጉ አካላት ከውጭ ብድር እና እርዳታ እንዳናገኝ ቢያደርጉም፣ ኢትዮጵያ በራሷ ልጆች ግድቡን ገንብታ ለፍፃሜ ማድረስ እንደቻለች የሚገልጹት ደግሞ ፓስተር ተስፋዬ ሀይሌ ናቸው።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በዘር፣ በቋንቋ፣ በጎሳ ሳንለያይ ልክ እንደ አድዋ በመተባበር ያሸነፍንበት እንደሆነ የሚገልጹት ፓስተር ተስፋዬ፣ ይህ በታሪክም ትልቅ ድል ያስመዘገብንበት ነው ብለዋል።

በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review