ከአሜሪካ-ሩሲያ የመሪዎች ጉባኤ በፊት ቫንስ እና ላሚ ስለ ዩክሬን ውይይት ማድረጋቸው ተገለፀ

You are currently viewing ከአሜሪካ-ሩሲያ የመሪዎች ጉባኤ በፊት ቫንስ እና ላሚ ስለ ዩክሬን ውይይት ማድረጋቸው ተገለፀ

AMN-ነሀሴ 4/2017 ዓ.ም

የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ እና የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ በዩክሬን ስላለው ጦርነት ከጸጥታ ባለስልጣናት ጋር በለንደን አቅራቢያ ዉይይት ማድረጋቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

በውይይቱ የዩክሬን ባለስልጣናት እና የአውሮፓ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ይህ ውይይት በአሜሪካ ጥያቄ የተደረገ መሆኑም ታውቋል።

የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ በበኩላቸው ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መስራታችንን እንቀጥላለን ሲሉ ተሰምተዋል።

የዩክሬን ብሄራዊ ደህንነት እና መከላከያ ምክር ቤት ፀሃፊ ረስተም ኡሜሮቭ ፣ የዜለንስኪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አንድሪይ ይርማክ ፣ከእንግሊዝ ፣ ከአውሮፓ ህብረት ፣ከፈረንሳይ ፣ከጀርመን ፣ከጣሊያን ፣ከፊንላንድ እና ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የተወከሉ ባለስልጣናት ውይይቱን መሳተፋቸው ታውቋል።

የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር ከስብሰባው በፊት ዘለንስኪ ጋር ተገናኝተው የተነጋገሩ ሲሆን፥ ወደ ሰላም የሚደረገውን ጉዞ ለመወያየት ወሳኝ መድረክ እንደሚሆን መስማማታቸው ተገልጿል።

ትራምፕ እና ፑቲን በበኩላቸው ነሀሴ 15 በሚያደርጉት ውይይት ስለ ጦርነቱ የወደፊት ሁኔታ ላይ ለመምከር መዘጋጀታቸውን ቢቢሲ ዘግቦታል።

የሰላም ስምምነቱን አስመልክቶ ትራምፕ አርብ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በሁለቱም በኩል አንዳንድ ግዛቶችን ይለዋወጣሉ ሲል ተናግሯል ።

በርካታ የአውሮፓ መሪዎች ዩክሬንን እንደሚደግፉ ቅዳሜ ምሽት የጋራ መግለጫ መስጠታቸው ተዘግቧል ።

የዩክሬኑ ኘሬዝዳንት ዘለንስኪ በበኩሉ ፣ በእንግሊዝ የተደረገው ውይይት ገንቢ መሆኑን የገለፀ ሲሆን የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኤክስ ገፃቸው ላይ ባስተላለፉት መልእክት ደግሞ፣ የዩክሬን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ከዩክሬናውያን ውጭ ሊወሰን አይችልም ብለዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዪክሬን ወታደሮች እና ሰላማዊ ዜጎች ለሰላም ያላቸውን ከፍተኛ ፍላጎት መግለፃቸው ታውቋል።

በብርሃኑ ወርቅነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review