የሴቶችን ተሳትፎንና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚሠራ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
የለውጡ ትሩፋት የሆኑ ሴት አመራሮች መድረክ “ሴት አመራሮች ለኢትዮጵያ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ በሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የተገኙት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ፣ በለውጡ ዓመታት ሴት አመራሮች ወደፊት እንዲመጡ በመደረጉ አመርቂ ውጤቶች መጥተዋል ብለዋል።
በቀጣይም ሴቶችን በኢኮኖሚ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ መደገፍ፣ የትምህርትና የክህሎት ደረጃን ማላቅ እንዲሁም ፖለቲካዊ ተሳትፎን ይበልጥ ማሳደግ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡
በዚህ መድረክ ተሳታፊ የሆኑ ሴት አመራሮች በቀጣይ አመራር የሚሆኑ ሴቶችን ለማፍራት እና ለማብቃት መስራት ይገባቸዋል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሴት አመራሮች ወደፊት እንዲመጡ በመደረጋቸው ኢትዮጵያ በሁለንተናዊ ዘርፍ ውጤት እንድታስመዘግብ ማስቻሉን ተናግረዋል።
በለውጡ ዓመታት የሴቶች ተሳትፎ የተሻለ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሯ፣ ሴቶች የመምራት ዕድል ከተሰጣቸው ያላቸውን ተሰጥኦ አውጥተው በመጠቀም የተሻለ ነገር ለሀገራቸው ማበርከት እንደሚችሉ ገልጸው፣ ባለፉት 7 የለውጥ ዓመታትም ይህ ነው የታየው ብለዋል።
የተዛቡ ትርክቶችን በማስወገድ የሀገረ መንግስት ግንባታ ማረጋገጥ እንዲቻል የሴት አመራሮችን ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል።
የሴቶች ፍትሀዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥም ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ይተጋል ሲሉም አክለዋል፡፡
ለሀገር ብልጽግና የሚጠቅሙ ሀሳቦችን በማፍለቅና ተግባራዊ ለማድረግ ሴት አመራሮች በየጊዜው ራሳቸውን ማብቃት ይገባልም ብለዋል።
መድረኩ በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተዘጋጀ ሲሆን፣ በመድረኩ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ ሚኒስትሮች እና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር ተገኝተዋል።
በሄለን ጀምበሬ