በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የዕጣን ምርት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡
የኮርፖሬሽኑ የኮሙኑኬሽንና ማኅበራዊ ኃላፊነት ሥራ አመራር ሥራ አስኪያጅ ጋሻው አይችሉህም እንዳሉት፤ 2ሺህ 505 ኩንታል ዕጣን ወደ ቻይና፣ ዱባይ፣ ግሪክ፣ ቱኒዝያና ቱርክ በመላክ ከ1 ሚሊየን 641 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡
በተጨማሪም 260 ኩንታል ዕጣን ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ ከ7 ሚሊዮን 710ሺህ ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ሲነጻጸር ብልጫ እንዳለውም ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከሚሰበስበው የዕጣን ምርት ከ90 በመቶ በላይ ያህሉን ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ አስታውቀዋል፡፡
በዘርፉ የሚስተዋል ሕገ-ወጥ ንግድ እና ሌሎች ተግዳሮቶች ሀገር ከተፈጥሮ ሙጫና ዕጣን ሽያጭ በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ እንዳትሆን ማድረጉን አመላክተዋል፡፡
በ2018 በጀት ዓመት 2ሺህ 510 ኩንታል የዕጣን ምርት ወደ ውጭ በመላክ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት መታቀዱን ጨምረው ጠቅሰዋል፡፡