ኢትዮጵያ ለምታስገነባው አዲስ ዓለም አቀፍ የኤርፖርት ከተማ የአፍሪካ ልማት ባንክ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ፋይናንስ የማስተባበር ሃላፊነት የወሰደበትን ስምምነት ከአየር መንገዱ ጋር ዛሬ ተፈራርሟል።
በሥነ-ስርዓቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ፣ የኢትዮጵያ አየር ሀይል ዋና አዛዥና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አኪንውሚ አዴሲና (ዶ/ር) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ሃላፊ ለማ ያዴቻ እንዲሁም የአየር መንገዱ እና የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ቢሾፍቱ አቅራቢያ አቡሴራ አካባቢ ለሚገነባው አዲስ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የፍላጎት መግለጫ ስምምነት ሰነድ በአቡጃ መፈረማቸው የሚታወስ ነው።
ይህንኑ ተከትሎ ባንኩ ለአየር መንገዱ አዲስ የኤርፖርት ግንባታ የፋይናንስ ምንጭ በማፈላለግ አስተባብሮ ለመስጠት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ሃላፊ አቶ ለማ ያዴቻና እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አኪንውሚ አዴሲና ፈርመዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እንደተናገሩት፤ በ10 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚገነባው ይህ ግዙፍ የኤርፖርት ፕሮጀክት አየር መንገዱ በራዕይ 2035 በዓለም ካሉ ተወዳዳሪ አየር መንገዶች ተርታ ለመሰለፍ የሚያደርገውን ጥረት በእጅጉ የሚደገፍ ይሆናል ብለዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ በዚህ ሂደት ቀጣናዊ ልማትን ለማፋጠን እየተወጣ ላለው ወሳኝ ድርሻም በኢትዮጵያ መንግስት ስም አመስግነዋል።
የአየር ሀይል ዋና አዛዥና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ አየር መንገዱ የሚያስገነባው አዲስ ኤርፖርት ሙሉ በሙሉ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ የአፍሪካ ብቻ ሳይሆን የአለም አንዱ የአቪዬሽን ማዕከል ይሆናል።

የአፍሪካ ልማት ባንክም በዚህ ወሳኝ የፕሮጀክት ግንባታ የፋይናንስ ምንጭ ለማፈላለግ ለወሰደው ሃላፊነትና ላሳየው ቁርጠኝነትም አመስግነዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አኪንውሚ አዴሲና፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢሾፍቱ አቅራቢያ ለሚያስገነባው ሜጋ ፕሮጀክት የአፍሪካ ልማት ባንክ የተሰጠውን ስምንት ቢሊዮን ዶላር ፋይናንስ የማስተባበር ሃላፊነቱን በሚገባ እንደሚወጣ ገልጸዋል።
የአፍሪካዊያን ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አህጉራዊ ትስስርን በማጠናከር እየተወጣ ላለው ድርሻም አመስግነዋል።
በጠቅላላው 10 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ ይደረግበታል ተብሎ የሚገመተው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በቢሾፍቱ ከተማ አቅራቢያ አቡሴራ የሚገነባ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድን አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድጋል ተብሎም ይጠበቃል።
የግንባታ ሂደቱ በሁለት ምዕራፍ የሚከናወን ሲሆን፤ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በዓመት ከ110 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም እንዳለዉ ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ኤርፖርቱ በአገር እና ዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ ለመጣው የመንገደኞች እና የካርጎ አገልግሎት ፍላጎት አጥጋቢ ምላሽ ይሰጣል ነው የተባለው።