ዝነኛዋ አሜሪካዊት ተዋናይት ፣ የፊልም ባለሙያ እና የሰብአዊ ድጋፍ አቅራቢ አንጀሊና ጆሊ የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ጎብኝታለች።
ተዋናይቷ ያደረገችው ጉብኝት በዋነኝነት ሆስፒታሉ እየሰጠ በሚገኘው መድሃኒቱን የተላመደ ቲቢ (ኤም.ዲ.አር ቲቢ) ህክምና ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉ እንቅስቃሴዎችን ፣ የሚታዩ ለውጦችን እንዲሁም ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ቦታዎች መለየት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ ናሆም ፍርድአወቅ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ ተናግረዋል፡፡
በጉብኝቱ ላይ አንጀሊና የሆስፒታሉን የቲቢና መድሃኒቱን የተላመደ ቲቢ (ኤም.ዲ.አር ቲቢ) ህክምና አገልግሎት መስጫ ዋርድ ፣ ላብራቶሪ እንዲሁም ታካሚዎችን ተዘዋውራ መመልከቷን ገልጸዋል፡፡
አንጀሊና ሆስፒታሉን ከረጅም ጊዜያት በፊት ጎብኝታ እንደነበር የገለጹት አቶ ናሆም ፍርድአወቅ በአሁኑ ጉብኝቷ ላይ ሆስፒታሉ ዘርፈ ብዙ ለውጦች ማምጣቱን መናገሯን ጨምረዉ ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም በቀጣይ በአለም ጤና ጥበቃ ኮሚቴ (Global Health Committee) በኩል ለሆስፒታሉ ድጋፍ እናደርጋለን ብላለች።
የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር አብርሃም እሸቱ በበኩላቸው ቲቢን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ተዋናይቷ ላሳየችው ዘላቂ ቁርጠኝነት፣ ልግስና እና በቀጣይ ለማድረግ ቃል ስለገባችው ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አንጀሊና ጆሊ ከፊልም ስራ ባሻገር በአለም ዓቀፍ ደረጃ ለስደተኞች እና ለሰብአዊ መብቶች ጥብቅና በመቆም በተባበሩት መንግስታት ስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የበጎ ፈቃድ አምባሳደር እንዲሁም ልዩ መልዕክተኛ በመሆን ከ20 ዓመታት በላይ በማገልገል በሰራችው ሰፊ የሰብዓዊነት ስራ ትታወቃለች።
በወንድማገኝ አሰፋ