ሰማንያ በመቶ የሚሆነው የልብ ጥቃት ህመም መከላከል ይቻላል

You are currently viewing ሰማንያ በመቶ የሚሆነው የልብ ጥቃት ህመም መከላከል ይቻላል

AMN – ነሐሴ 6/2017 ዓ.ም

“የኸርት አታክ” ኢትዮጵያ መስራች እና የልብ ሃኪም ናቸው ዶክተር ተስፋዬ ተሊላ፡፡

ባለፉት ስምንት ዓመታት በፒልሞን ኸርት ኢንስቲትዩት ኢንተርቬንሽናል ካርዲዮሎጂስት ቀዶ ህምክና ሳያስፈልገው የሚደረግ በትንንሽ የደም ቧንቧዎች በመታገዝ የተዘጉ የልብ ቧንቧዎችን እና ቫልቮችን መክፈት ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ የህክምና ባለሞያ ናቸው፡፡

ቀዶ ጥገና ሲባል መቅደድ አለ፣ የተበላሸውን ነገር ማስተካከል እንዲሁም መዝጋት አለ፡፡ ይህ የህክምና ዓይነት ከድሮ ጀምሮ ማለትም ከፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1960ዎቹ ጀምሮ ሲሰራበት የነበረ የህክምና ዘዴ መሆኑን ነው ዶክተር ተስፋዬ የሚናገሩት፡፡

አሁን ላይ ነገሮች እየተሻሻሉ እና እየዘመኑ መምጣታቸውን የሚያነሱት ዶከተር ተስፋዬ፣ ልብን ለማከም ሌላኛውን የሰውነት አካል ሳይቀዱ መጠገን/ ኢንተርቬንሽናል ካርዲዮሎጂ/ በትንንሽ ቀዳዳዎች ወደ ሰውነት ገብቶ የሚደረግ ወይንም የሚሰጥ ህክምና ነው፡፡

ታዲያ የሚጠቀሙበት የህክምና መሳሪያ ከመራቀቁ ውጭ ህክምናው ተመሳሳይ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ተስፋዬ፣ በዚህ ዘዴ ህክምና ያገኙ ዜጎችም በሁኔታው በመገረም ታዲያ እንዴት ሰራቸሁኝ ሲሉ የሚጠይቁ ታካሚዎች መኖራቸውን ጭምር በማንሳት ገጠመኛቸውን አውስተዋል፡፡

በዚህ የክህምና ዓይነት የሚታከሙ ታካሚዎች ለማገገምም ጊዜ እንደማይወስድባቸው ገልፀው፣ ነገር ግን ህክምናው በቀዶ ጥገና የተደረገ ቢሆን ቁስለቱ እና ህመሙ ስላለ እስኪያገግሙ ድረስ ሶስት አራት ቀን እንዲሁም ሳምንታት በህክምና ሊያሳልፉ እንደሚችሉ ነው የገለጹት፡፡

አሁን ላይ ያለው የልብ ህክምና የሰውነትን አካል ቀዶ ህክምና ማድረግ ሳያስፈልግ በተራቀቀ የህክምና መሳሪያ ውጤቶች ማከም እንደተቻለም ያብራራሉ ፡፡

ይህ ሳይቀዱ መጠገን /ማከም/ የህክምና ዓይነት፣ ለሁሉም ታካሚዎች የሚሰጥ አለመሆኑንና ህክምናው የሚሰጠው እንደ ታካሚው የጤና፣ የዕድሜ ሁኔታና የበሽታ ደረጃ የሚወሰን መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ይህ ህክምና ውድና ከፍተኛ ወጭ የሚጠይቅ በመሆኑ ለሁሉም ታካሚዎች ለመስጠት አዳጋች መሆኑን የሚናገሩት ዶክተሩ፣ ነገር ግን እሳቸውና ማህበራቸው ህብረተሰባቸውን ተጠቃሚ ለማደረግ፣ ይህንን ህክምና ተግባራዊ በማድረግ ብዙዎችን ከልብ ህመም መታደግ መቻላቸውን ገልፀዋል፡፡

80 በመቶ የሚሆነው የልብ ጥቃት ህመም በህክምና መከላከል የሚቻል መሆኑን የገለፁት ባለሞያው፣ ነገር ገን የማህበረሰቡ የግንዛቤ ደረጃ ማነስ እንዲሁም የዘርፉ ባለሞያዎች በቂ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ በተለይ በሚዲያ በቂ ስራ አለመሰራቱ ችግሩ እንዲባባስ ማድረጉን አመላክተው፣ በቀጣይ ግንዛቤ መፍጠር ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባው ገልፀዋል፡፡

የተዘጋ የደም ቧንቧ ችግር ኖሮን ነገር ግን የህመም ሰሜቱ ላይኖረን ይችላል የሚሉት ዶክተር ተስፋዬ፣ አለማጨስ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የኮሌስትሮል እና የደም ግፊትን ማወቅ እና የህክምና ክትትል በማድረግ እንደሚገባም መክረዋል፡፡

በተጨማሪም የደም ቧንቧ ችግር ለመፈጠሩ ምክንያት ሳይታከም የቀረ የቶንሲል ህመም መሆኑን ገልፀው፣ በተለይ ህፃናት ቶንሲል ሲይዛቸው ቶላ ማሳከም እና በተደጋጋሚ በቶንሲል እንዳይያዙ ማድረግ ይገባል ሲሉ የሙያዊና የዜግነታዊ ሃላፊነታቸውን መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review