“የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሼቲቭ” የኮንስትራክሽን ዘርፉ ያሉበትን ችግሮች ቀርፎ የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ተዋንያን በጎረቤት እና የአፍሪካ ሀገራት የመስራት አቅም እንዲኖራቸው እንደሚያስችል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገልጸዋል።
“የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሼቲቭ” የማስጀመሪያ መርሐ-ግብር እየተካሄደ ነው።
በመርሐ-ግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ኢኒሼቲቩ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ያሉበትን ችግሮች ቀርፎ የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ተዋንያን በጎረቤትና የአፍሪካ ሀገራት የመስራት አቅም እንዲኖራቸው እንደሚያስችል ገልፀዋል።

ከ2025 እስከ 2050 ቆይታ የሚኖረው ኢኒሼቲቩ፣ ኢትዮጵያ በዘርፉ ተወዳዳሪ እንድትሆን ከማስቻል ባሻገር ዘርፉ ከዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጋር እኩል እንዲራመድም መደላድልን የሚፈጥር ስለመሆኑ ተነግሮለታል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፣ የኮንስትራክሽን መስኩ በሰው ሰራሽ አስተውህሎትና ቴክኖሎጂ ማደራጀት የኢኒሼቲቩ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ከውጭ እያስገባቸው የሚገኙ ግብዓቶች በሀገር ውስጥ ምርት እንዲተኩ የማድረግ ስራ የኢኒሼቲቩ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች ስለመሆናቸው አብራርተዋል።
የኮንስትራክሽን ተቋራጭና አማካሪዎች ራሳቸውን አብቅተው ወደሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ወጥተው እንዲሰሩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
በመርሐ-ግብሩ የአፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት፣ ዓለም ዓቀፍ እና ሀገር በቀል የኮንስትራክሽን ተቋራጮችን ጨምሮ የተለያዩ የዘርፉ ተዋንያን ታድመዋል።
በመቅደስ ደምስ