ቤት አልባው ብራዚላዊ ኢሳቅ ዶ ሳንቶስ ፒኖህ፣ የ8 ኪሎ ሜትር ውድድርን በነጠላ ጫማ በመሮጥ ርቀቱን ማጠናቀቁ የበርካቶችን ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኗል፡፡
ኢሳቅ ዶ ሳንቶስ ሳይመዘገብበት ድንገት የተሳተፈበት የሩጫ ውድድር የሕይወቱን አቅጣጫ እንደሚቀይር አላሰበውም ነበር፡፡
ኢሳቅ ዶ ሳንቶስ ፒኖህ ያደገው በእናቱ ጉያ ነው፡፡
አባቱ በልጅነቱ ትቷቸው ስለሄደ እጅግ አስቸጋሪ የሆነ የህይወት መንገድ ውስጥ ማለፉ ለተስፋ መቁረጥና ከባድ ለሆነ የአልኮል መጠጥ ሱሰኝነት ዳርጎታል፡፡
ታዲያ ቤት አልባው የ31 ዓመቱ ወጣት ከሁለት ሳምንታት በፊት በትውልድ ከተማው ጋራፎ ዶ ኖርቴ የሩጫ ውድድር ሲካሄድ የተመለከተውም በመጠጥ ቤት ውስጥ ሆኖ ነበር፡፡
በወቅቱም አትሌቶች እና በርካታ የከተማውን ነዋሪዎች በውድድሩ ስፍራ ይመለከታል፡፡
ኢሳቅ ዶ ሳንቶስ ሩጫ ከመጠጥ በኋላ የሚመጣውን የድባቴ ህመም ወይም (የሀንግኦቨር) ስሜት እንደሚከላከል ግንዛቤው ስለነበረኝ ወዲያው ከመጠጥ ላይ ተነስቼ ወደ ውድድሩ ሜዳ ገባሁኝ ይላል፡፡
በውድደሩ ተሳታፊ ለመሆን አስቀድሞ አልተመዘገበም፡፡ ለሩጫ የሚሆኑ ትጥቆችንም አልተዘጋጀባቸውም፡፡
በመሆኑም እንደነገሩ ለብሶት በነበረው ልብስ እና በተጫማው ነጠላ ጫማ፣ የ8 ኪሎ ሜትር ሩጫውን ከፊት ሆኖ እየመራ ተጉዟል፡፡
ይሁንና እስከ መጨረሻው መምራት ባይችልም እርቀቱን ማጠናቀቅ መቻሉ በራሱ የበርካቶችን ቀልብ መያዝ ችሏል፡፡
የብራዚል መገናኛ ብዙሀንም “ሯጩ ኢሳቅ” በሚል ርዕስ ዘገባዎችን ይዘው የወጡ ሲሆን፣ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃንም በርካቶች በስፋት የተመለከቱት ጉዳይ ሆኗል፡፡
ከእንግዲህ የአልኮል መጠጥ አልጠጣም ምክንያቱም ሩጫውን እሮጬ አጠናቂቅያለሁና ያለው ኢሳቅ፣ ብዙ ምክርም ስላገኘሁ ተስፋ አልቆርጥም ሲል ነው ለጋዜጠኞች የተናገረው፡፡
የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎችም የወጣቱ ሕይወት እንዲቀየር ልዩ ልዩ ድጋፎችን እያመቻቹለት ይገኛል፡፡
እስካሁንም የስፖርት ትጥቅ፣ አልባሳት፣ ልዩ የመሮጫ መነፅር እና ከእውቅ አትሌቶች ጋር ልምምድ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቦለታል፡፡
የጋራፋኦ ዶ ኖርቴ ከተማም በቀጣይ በሚካሄዱ የሩጫ ውድደሮች ላይ ተሳታፊ እንዲሆን ኢሳቅ ዶ ሳንቶስን ከወዲሁ ጋብዞታል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ኢሳቆ ዶ ሳንቶስን ከጎዳና ላይ በማንሳት የመኖሪያ ቤት እንዲገነባለት በማህበረሰብ አንቂዎች በኩል በስፋት እየተሰራ እንደሚገኝ ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡
በማሬ ቃጦ