በቀጣናው የዓሣ ምርትና ንግድን ዘመናዊና ቀልጣፋ እንዲሆን የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አስታወቀ

You are currently viewing በቀጣናው የዓሣ ምርትና ንግድን ዘመናዊና ቀልጣፋ እንዲሆን የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አስታወቀ

AMN ነሃሴ 6/2017

ኢጋድ በቀጣናው የዓሳ ሀብት ልማት ላይ ያተኮረ ከፍተኛ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ በማካሄድ ይገኛል።

በኢጋድ የግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ዳይሬክተር ዳሄር ኤልሚ ሁሴን በዚሁ ወቅት እንዳሉት በተደረጉ ጥናቶች መሰረት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ዓመታዊ የዓሳ ሃብት አቅም ከፍተኛ ቢሆንም የሚመረተው ምርት ግን ዝቅተኛ ነው።

ይህም የቀጣናው እምቅ ሀብት በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ እንዳልዋለ እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

የቀይ ባህር፣ ሕንድ ውቅያኖስ፣ የዓባይ ወንዝ፣ የቪክቶሪያና የቱርካና ታላላቅ ሐይቆች በሚሊዮን የሚቆጠሩ የምስራቅ አፍሪካ ዜጎችን በስራ ዕድልና በምግብ ዋስትና እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

በሶማሊያ፣ በጅቡቲና በኬንያ የባህር ዳርቻዎች ያለውን የዓሣ ሀብት ለቀጣናው የንግድና የምግብ ዋስትና ትልቅ አቅም መሆን በሚያስችል መልኩ ማልማት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

የቀጣናውን ሀገራት ዝቅተኛ የዓሣ ምርታማነት ለማሻሻል ከአውሮፓ ሕብረት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በሁለት ተሻጋሪ የውሃ ካላት ላይ የሙከራ ፕሮጀክት እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሀገራትም የዓሣ ምርትን በዘመናዊ ቀልጣፋ የንግድ ሥርዓት እንዲመራ ለማስቻል የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የዓሣ ሀብት እና የብሉ ኢኮኖሚ ልማት በኢጋድ የአምስት ዓመት ስትራቴጂና እስከ 2050 ባለው የኢጋድ የለውጥ አጀንዳ ቁልፍ ከሆኑ ዘርፎች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢጋድ አባል ሀገራት የራሳቸውን ብሔራዊ የውሃ አካላት (ብሉ ኢኮኖሚ) ስትራቴጂ በማዘጋጀት የዘርፉን ዕድገት ለማፋጠን በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከድንበር ተሻጋሪ ወንዞቿ እና ሀይቆቿ የሚመነጭ ከፍተኛ የዓሣ ሀብት አላት ብለዋል።

የኢትዮጵያ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የዓሣ ሃብት ምርታማነትን በማሳደግ ከፍተኛ እመርታ እንዲመዘገብ እያስቻለ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዓባይ ወንዝ ላይ ተገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለዓሣ ሃብት ምርታማነት ከፍተኛ አስታጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ ለኢጋድ ብሉ ኢኮኖሚ አጀንዳ እና የዘላቂ የዓሣ ሀብት ስትራቴጂ ጽኑ አቋም እንዳለት ገልጸዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review