ማቲያ ዴቤርቶሊስ ስፖርት አብዝቶ የሚወድ የ29 ዓመት ጣልያናዊ ሲሆን፣ አካል እና አእምሮን የሚፈትነውን ኦሪኤንተሪንግ ስፖርትን ለመሳተፍ ወደ ቻይና ቼንግዱ ከተማ ቢያቀናም በሕይወት አልተመለሰም፡፡
ኦሪኤንተሪንግ የሰውን ልጅ የመቻል ብቃት የሚፈታተኑ የተለያዩ ስፖርቶችን ያቀፈ የውድድር ዓይነት ነው፡፡
በዚህ ውድድር ተሳታፊዎች ማጠናቀቂያ ቦታው ምልክት ስለሌለው ካርታ እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ለመያዝ ሁሉ ይገደዳሉ፡፡
ዓለም አቀፍ ኦሪኤንቲንግ ፌዴሬሽን (IOF) የተቋቋመለት ኦሪኤንቲንግ በየአራት ዓመቱ ይካሄዳል ፡፡
ለውድድር የተመረጡት የስፖርት ዓይነቶቹ በኦሊምፒክ የተካተቱ አይደሉም፡፡
ይህን አስቸጋሪ ስፖርት ለመካፈል ቻይና ያቀናው ማቲያ ዴቤርቶሊስ ባሳለፍነው አርብ የተራራ ላይ ሩጫ በሚያደርግበት ወቅት ተዝለፍልፎ ይወድቃል፡፡
በውድድሩ ወቅት የሙቀት መጠኑ ከ30 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እንደነበር ቢቢሲ በዘገባው ጠቅሷል፡፡
ከወደቀ በኋላ መንቃት ያልቻለው ማቲያ ለአራት ቀናት ህክምና ቢከታተልም ሕይወቱ ልትተርፍ አልቻለችም፡፡
ማቲያ ዴቤርቶሊስ በኦሪኤንተሪንግ ስፖርት ልምድ ያለው እና ሀገሩንም በተለያዩ አጋጣሚውች ወክሎ የተወዳደረ ነበር፡፡
በ2022 ከሀገሩ ልጆች ጋር በቡድን ተሳትፎ አምስተኛ ወጥቶ እንደ ነበር ዘገባው አስታውሷል፡፡
የምህንድስና ሙያም ባለቤት እንደሆነ የተነገረለት ማቲያ፣ ምንም እንኳን የጣልያን ዜግነት ይኑረው እንጂ፣ ኑሮውን በስዊድን ነበር ያደረገው፡፡
በስቶክሆልም ዩኒቨርሲቲም ፒ ኤች ዲውን እየተማረ ነበር፡፡
ዓለም አቀፍ ኦሪኤንቲንግ ፌዴሬሽን የማቲያ ዴቤርቶሊስ ህልፈት ከሰማ በኋላ የሃዘን መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ ቤተሰቦቹን ለመደገፍ ሁሌም ዝግጁ እንደሆነ አሳውቋል፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ