ቲክቶክን በመጠቀም ግጭት ቀስቃሽ መረጃ ሲያሰራጩ የነበሩ አምስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸዉን ፖሊስ አስታወቀ

You are currently viewing ቲክቶክን በመጠቀም ግጭት ቀስቃሽ መረጃ ሲያሰራጩ የነበሩ አምስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸዉን ፖሊስ አስታወቀ

AMN ነሃሴ 6/2017

ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የከተማዋን ሠላም ለማወክ እና በህብረተሰቡ ላይ የደህንነት ስጋት ለመፍጠር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን እንደማይታገስ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታዉቋል፡፡

አዲስ አበባ ከወንጀል የፀዳች እንድትሆንና ዜጎች በሠላም ወጥተው በሠላም እንዲገቡ የአዲስ አበባ ፖሊስ የመዲናዋን ነዋሪዎች ባሳተፈ መልኩ ቴክኖሎጂ መር የሆኑ የወንጀል መከላከልና ምርመራ ስራዎችን በማከናወን በርካታ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል፡፡

ዜጎች ሠላምና ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን በተከናወኑ አመርቂ ስራዎች ባሳለፍነው በጀት ዓመት በከተማዋ የወንጀል ምጣኔን 43 በመቶ መቀነስ መቻሉን ፖሊስ አስታዉቋል፡፡

የሚፈጸሙ ወንጀሎችን እጅ ከፍንጅ የመያዝ አቅሙን በማሳደግ እና ዜጎች በቀጥታ ለፖሊስ መረጃ የሚሰጡበትን መንገድ (የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ አፕሊኬሽን ) በማመቻቸት ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝም የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅሷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ (ቲክቶክ) ፕላትፎርምን በመጠቀም የከተማዋን ሠላም ለማወክ እና በህብረተሰቡ ላይ የደህንነት ስጋት ለመፍጠር በተደራጀ መንገድ በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች እና ቡድኖች ላይ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ እንደሆነም አስታውቋል፡፡

ፖሊስ በክትትል ከደረሰባቸው መረጃዎች በተጨማሪ የህብረተሰቡን ጥቆማ መነሻ በማድረግ በህብረተሰቡ እና በከተማችን ላይ የደህንነት ስጋት ለመፍጠር በማሰብ ቲክቶክን በመጠቀም የተለያዩ መልዕክቶችን ሲያሰራጩ የነበሩ ኪሩቤል መላኩ ፣ አህመድ ሻሂር ፣ ምኺኤል አብይ፣ በረከት ዳንኤል እና አብዩ ደግአረገ የተባሉ አምስት ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡

ይህንን የቲክቶክ ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ከህብረተሰቡ ስነ ልቦና ተቃራኒ የሆኑ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ ከነበሩት እና በአሁኑ ወቅት በፖሊስ ክትትል እየተደረገባቸው ከሚገኙት መካከል አንዱ ብሩክ ተስፋዬ አርአያ የሚባል ግለሰብ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

ይህ ግለሰብ ነዋሪነቱ በየካ ክ/ከተማ ሲግናል የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሲሆን ከዚህ ቀደም በህግ የተከለከለን “ካናቢስ” የተባለ አደንዛዥ ዕጽ ይዞ በመገኘት ወንጀል ክስ ቀርቦበት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ 2ኛ አርቲዲ ወንጀል ችሎት ቀርቦ የዋስትና መብት ከተፈቀደለት በኋላ በቀጠሮ ቀን ሳይቀርብ ተሰውሮ በመቆየቱ ፍርድ ቤቱ በሌለበት ታህሳስ 23 ቀን 2017 ዓ/ም በዋለው ችሎት ጥፋተኛነቱን በማረጋገጥ በአንድ ዓመት ጽኑ እስራትና በአንድ ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኖበታል።

ተከሳሹ ይህ ውሳኔ ከተላለፈበት በኋላም ራሱን በመሰወር በማህበራዊ ሚዲያ (ቲክቶክ) የቀጥታ ስርጭት በተደጋጋሚ ጊዜ ከህብረተሠቡ ስነ ልቦና ተቃራኒ የሆኑ መልዕክቶችን እያስተላለፈ የሚገኝ በመሆኑ ጭምር በፖሊስ እየተፈለገ ይገኛል፡፡

እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች የመዲናችንን ነዋሪዎች ደህንነት ስጋት ውስጥ የሚከቱና ድርጊቱ በቸልታ ከታለፈም ትልቅ አደጋ ሊያመጣ የሚችል በመሆኑ የድርጊቱን ፈፃሚዎች እንደማይታገስ ያስታወቀው የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ፤ መሠል እንቅስቃሴ በሚያደርጉ የማህበራዊ ሚዲያ አንቂ ነን ባዮች ላይም ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ፖሊስ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በላከዉ መረጃ አስታዉቋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review