የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንደተቀናቃኝ ሳይሆን አካታች፣ የበለፀጉ እና ሰላማዊ ሃገራትን ለመገንባት እንደመሳሪያ መጠቀም እንደሚገባ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለፁ።
12ኛው የአፍሪካ ፓለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ በጋና አክራ “ከፖለቲካ ወደ ብልፅግና፡ ለአፍሪካ እድገት እና የኢኮኖሚ ሽግግር በፓርቲዎች መካከል ትብብርን በማጠናከር” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በመድረኩም የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ እና የብልፅግና ፓርቲ ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በመድረኩ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ አደም ፋራህ፣ የጉባኤው መሪ መልዕክት በራሱ የአፍሪካ የወደፊት እጣ ፈንታ በፖለቲካ መሪዎች ውሳኔ ላይ የተመረኮዘ እንደሆነ ማሳያ ነው ብለዋል።
ለረጅም ጊዜያት በብዙዎቻችን ሃገራት ፖለቲካ በስልጣን ሽኩቻ፣ በአጭር ጊዜ አጀንዳዎች እና የሃገርን ጉልበት በሚያሟጥጥ ፉክክር ይመራ ነበር ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ የአንዱ ሽንፈት የአንዱ ድል ነው የሚለውን አስተሳሰብ በመሻገር የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንደተቀናቃኝ ሳይሆን አካታች፣ የበለፀጉ እና ሰላማዊ ሃገራትን ለመገንባት እንደመሳሪያ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።
ይህ ለውጥ ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ተሐድሶ ጠቅሟል ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ የ ‘’መደመርን’’ መርህ አንግበን እተጓዝን ነው ብለዋል።
በዚህም የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በተለያዩ መንግስታዊ የአስተዳደር ሂደቶች ውስጥ የማሳተፍ፤ ውጤቱ አንድነት እና ዘላቂ ልማት የሆነውን ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት መሆኑን ተናግረዋል።
በሊያት ካሳሁን