የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ትውልድ ግንባታ ላይ በአጽንኦት መስራት እንደሚያስፈልግ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ገለፁ።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ለ2018 የትምህርት ዘመን የትምህርት ግብአት አቅርቦትን ጨምሮ በቂ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል።
የቢሮው ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ(ዶ/ር) የተማሪዎች ዩኒፎርም የምርትና የስርጭት ሒደትን ተመልክተዋል።
እንደ ቢሮ በዘጠና ቀናት እቅድ ውስጥ ትምህርት ከመጀመሩ አስቀድሞ የመማሪያ ግብአትን በሁሉም ት/ቤቶች ለማድረስ በተሰራዉ ስራ እቅዱን በተጨባጭ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የትምህርት ግብአትን በጊዜ ተደራሽ ማድረግ ላይ የሚታየው ችግር የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማ እንዳይሆን እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል ያሉት ኃላፊው፤ ዛሬ ላይ ይህ ችግር መቀረፉን ገልጸዋል።

እንደ አዲስ አበባ ከተማ ትውልድ ግንባታ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ባለው ስራ ምገባና ዩኒፎርምን ጨምሮ ሁሉንም አስፈላጊ ግብአት ለተማሪዎች በነጻ እንዲቀርብ መደረጉ የተማሪዎችን ትምህርት ማቋረጥ በመቀነስ ትምህርት የመቀበል አቅምን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ የበቃና ንቁ ትውልድን ማፍራት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
መዲናዋ ይህንን ትውልድ ላይ የሚሰራው ስራን ለማሳካት የህዝቡና የግብር ከፋዩ ማህበረሰብ አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ዘላለም፤ የተጀመሩ ስራዎችን በማላቅ ትውልድ ግንባታ ላይ የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
በ2018 የትምህርት ዘመን የመንግስት ት/ቤቶችን ለሚመርጡ ተማሪዎች የመማሪያ ግብአትን በነጻ በማቅረብ የተሳካ የትምህርት አመትን ለማሳለፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።
በሔኖክ ዘነበ