ከ65 ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሐድሶ ሂደት አልፈው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን ኮሚሽኑ አስታወቀ

You are currently viewing ከ65 ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሐድሶ ሂደት አልፈው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን ኮሚሽኑ አስታወቀ

AMN ነሐሴ 6/2017

የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን 65ሺህ 500 የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሃድሶ ሂደት በማሳለፍ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረጉን ገለጸ።

የፌዴራል መንግሥት የቀድሞ ታጣቂዎችን ለማሰልጠን፤ ለስልጠና ማዕከላት ጥገና፣ ለምግብ፣ ለአልባሳት እንዲሁም ለተለያዩ ጉዳዮች እስከአሁን አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ማውጣቱ ተጠቁሟል።

የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ኮሚሽኑ እስካሁን ያከናወናቸውን ጉዳዮች በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ኮሚሽኑ 65ሺህ 500 የቀድሞ ታጣቂዎች በተሐድሶ ሂደት አልፈው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረጉን ገልጸዋል።

እነዚህ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት የመጡት ትጥቅ የማስረከብ፣ የማረጋገጥ፣ ምዝገባ የማካሄድ፣ የተሀድሶና የስነ ልቦና ሥልጠና በመውሰድ እንዲሁም የዲጂታል መታወቂያ አግኝተው ወደ ህብረተሰቡ የተቀላቀሉ መሆናቸውም ተጠቁሟል።

የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን እንደተናገሩት፤ ኮሚሽኑ የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊና ምርታማ ህይወት ለማሸጋገር በርካታ ስራዎችን አከናውኗል።

ኮሚሽኑ በሰላም ስምምነት እንዲሁም በመንግስት፣ በሀገር ሽማግሌዎችና በሀይማኖት አባቶች የቀረቡ ጥሪዎችን ተቀብለው ወደ ሰላም የሚመጡ የቀድሞ ታጣቂዎች የሀገሪቱ የሰላምና የልማት ኃይል እንዲሆኑ ለማስቻል እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከህዳር 12 ቀን 2017 ዓ.ም ወዲህ ከ65ሺህ 500 የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሃድሶ ሂደት በማሳለፍ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን ጠቁመዋል።

ይህም በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች መሆኑንም ማስታወቃቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review