የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ: የአዲስ አበባ ከተማ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ: የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን: የ11ዱ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ኃላፊዎች በተገኙበት የመዲናዋን ሠላምና ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግ ትኩረት በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሄዷል።
በመዲናዋ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ከማድረግ አንፃር የፀጥታ እና የወንጀል ስጋቶችን በመለየት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ገልጸዋል።
በ2018 በጀት ዓመት በከተማዋ የሚከናወኑ ህዝባዊም ሆነ ኃይማኖታዊ ኩነቶች በሠላም እንዲከናወኑ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በተሻለ አቋም ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑንም አንስተዋል።
በነሐሴ ወር 2017 ዓ/ም የሚካሄደው የመጅሊስ ምርጫ ሠላማዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ በየአካባቢው ምርጫ የሚደረግባቸው ቦታዎችን በመለየት ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በተለያዩ ክፍለ ከተሞች መረጃን መሠረት በማድረግ የፀጥታ ስጋት የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት የፍተሻና አሰሳ ስራ ተከናዉኗል።
በተከናወነዉ ስራም የፀረ ሠላም ኃይሎችን እና በልዩ ልዩ የወንጀል ተግባራት ላይ የተሰማሩ በርካታ ተጠርጣሪዎችን እንዲሁም ማህበራዊ ሚዲያን ተጠቅመው ተገቢ ያልሆኑ ግጭት ቀስቃሽ ሀሳቦችን የሚያሰራጩ ግለሰቦችን ጭምር በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝም ጨምረዉ ገልጸዋል።
ይህንም መነሻ በማድረግ ወሬና አሉባልታን እየፈበረኩ አጀንዳን የሚፈጥሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባም ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው አሳስበዋል።
በከተማዋ የሚደረገው የፍተሻና ቁጥጥር ተግባርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ከልዩ ልዩ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የመዲናዋን የፀጥታ ሁኔታ ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
ህዝቡና አመራሩ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም አካባቢውን መጠበቅ እንደሚኖርበት መግለጻቸዉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በላከዉ መረጃ አስታዉቋል።