የአንድ አመት ከስምንት ወር እድሜ ያለውን ህፃን በማገት ሁለት ሚሊዮን ብር የጠየቁ እና በወንጀሉ ተባብረዋል የተባሉ አራት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸዉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ፡፡
ወንጀሉ የተፈፀመው ሀምሌ 30 ቀን 20017 ዓ/ም በግምት ከምሽቱ 1፡40 ሰዓት ገደማ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው አፍሪካ ህብረት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መሆኑን ፖሊስ አስታዉቋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ፋኑኤል ብርሃነ የተባለን የ1 አመት ከ8 ወር ዕድሜ ያለውን ህፃን ከመኖሪያ ቤቱ በስውር በመውሰድ ወደ ወላጅ አባቱ ስልክ ደውለው ህፃኑን እንዳገቱት በመግለፅ እና ሁለት ሚሊዮን ብር በአካውንት ገቢ እንዲያደርጉ በመጠየቅ በቤተሰብ ላይ ጭንቀትና ድንጋጤን ፈጥረዋል፡፡ አቶ ብርሃነ ገ/ፃዲቅ የተባሉት የህፃኑ ወላጅ አባትም ስለ ሁኔታው በአቅራቢያቸው ለሚገኝ ፖሊስ በወቅቱ አሳውቀዋል።
የህፃኑ መጥፋት ሪፖርት የደረሰው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የቄራ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የምርመራ እና የክትትል ክፍሉ ተቀናጅተው በተደረገ ከፍተኛ ጥረት ካህሳይ ተክላይ የተባለውን እና ከህፃኑ ወላጅ አባት ጋር ዝምድና ያለውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ፖሊስ አስታዉቋል፡፡

የወንጀሉ አቀነባባሪ ነው ተብሎ ተጠርጥሮ በተያዘው በካህሳይ ተክላይ ላይ በተከናወነ ምርመራ የማስፋት ስራ በህፃኑ እገታ ከሚገኝ ገንዘብ የጥቅም ተካፋይ ለመሆን በመስማማት ወንጀሉን የተባበሩ ፊሊሞን ገ/ማርያም፣ ተክሊት ህሉፍ እና ምህረት ዕድሉ የተባሉ ተጨማሪ ሶስት ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
እነዚህ ተጠርጣሪዎች የተያዙት ወንጀሉ በተፈፀመ በማግስቱ ሳሪስ አካባቢ በሚገኘው ማራኪ በተባለ ሆቴል ውስጥ አልጋ ክፍል በመከራየት ህፃኑን ይዘው በተሸሸጉበት ወቅት ፖሊስ ባደረገው ክትትል ነው፡፡ በአጠቃላይ በወንጀሉ የተጠረጠሩት አራት ግለሰቦች በአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ፖሊስ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ በላከዉ መረጃ አስታዉቋል፡፡