የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል ጥምረት በፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂ የሶላር ሚኒግሪድና የሶላር ፓርክ ፕሮጀክት ግንባታ ማስጀመሪያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
የሁለትዮሽ የትብብር ስምምነቱ በፀሐይ ኃይል ፓርክና የሶላር ሚኒ ግሪድ የኃይል ማመንጫ፣ በመስኖና መጠጥ ውሃ አቅርቦትን የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ትብብር ዕድሎችን የሚያመቻች መሆኑ ተገልጿል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ የፀሐይ ኃይል የማመንጨት ከፍተኛ አቅም ቢኖራትም በእስካሁኑ ሂደት ጥቅም ላይ ያዋለችው ከ10 ሜጋ ዋት በታች ነው ብለዋል።
ከዋና የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ርቀው የሚገኙ መንደሮችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው እየተተገበሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ከዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል ጥምረት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር የሚደረገው የትብብር ስምምነትም የኃይል አቅርቦት ተደራሽነትን ለማስፋት ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ መሆኑን አስታውቀዋል።
በስምምነቱም ግብርናን በማዘመን በፀሐይ ኃይል የሚሰራ ከአየር ብክለት የጸዳ ቴክኖሎጂ ትግበራን ጨምሮ ልዩ ልዩ የአቅም ግንባታና የፀሐይ ኃይል ልማት ተደራሽነትን ለማስፋፋት እንደሚረዳ አንስተዋል።
የ400 ሜጋ ዋት የፀሐይ ፓርክ እና የፀሐይ ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክት ውጥኖችን በማሳካት የኢትዮጵያን የገጠር ኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ማስፋት የሚያስችል መሆኑንም አክለዋል።
ኢትዮጵያ ለዘላቂ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ምቹ ምኅዳር በመፍጠር ሁሉም ዜጎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አስቻይ ሁኔታ እየፈጠረች እንደምትገኝ መግለጻቸዉን ተዘግቧል፡፡