በአፋር ክልል ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን እስከ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን እድሜ ያለው አዲስ የአውስትራሎፒቲክስ ቅሪተ አካል ማግኘቱን የአሪዞና ስቴት ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ቡድን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን እና የአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ ሳይንቲስቶች እና የተመራማሪዎች ቡድን ግኝቱን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፥ የምርምር ቡድኑ በአፋር ሌዲ ገራሩ በተባለው ቦታ በርካታ ጉዞዎችን እና ቁፋሮዎች ያገኛቸውን ውጤቶች ይፋ ማድረጉን ገልጸዋል።
እነዚህ አዲስ የአውስትራሎፒቲከስ ዝርያ ጥንታዊ ግኝቶች ለኢትዮጵያና ለዓለም የሳይንስ ማህበረሰብ ትልቅ ጠቀሜታ አላቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ቅርስን ጨምሮ ለአርኪኦሎጂ እና ፓሊኦአንትርፖሎጂ ምርምር ትኩረት መስጠቱን ጠቅሰው፥ ከምርምር ተቋማት ጋር ትብብሩን አጠናክረው እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ለዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሰሩ እና የኢትዮጵያን የሰው ዘር መገኛነት በምርምራቸው ለዓለም ላሳዩ ተመራማሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።
የተመራማሪ ቡድኑ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ኤሚ ሬክተር የአዲሱ የአውስትራሎፒቲከስ ቅሪተ አካል ግኝት ዕድሜ ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን እስከ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዓመት መሆኑን መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።
ግኝቱ የኢትዮጵያን የሰው ዘር መገኛነት የሚያጠናክር አዲስ መረጃ የሚሰጥ ነው ብለዋል።