የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱ በገበያ እንዲመራ መደረጉ አብዛኛው የውጭ ምንዛሬ በባንኮች እንዲላክ ማስቻሉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ ገለጹ።
አምባሳደር ፍጹም ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሬሚታንስ ከሰባት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አግኝታለች።
ይህም ኢትዮጵያ ከሬሚታንስ ያገኘችው ትልቁ ገቢ መሆኑን ገልጸው በ2016 ዓ.ም ማብቂያ ላይ የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱን በገበያ እንዲመራ መደረጉ ከባንክ ውጪ የሚላከውን ገንዘብ በመቀነስ አብዛኛው በባንኮች እንዲላክ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።
ካለው አቅም አንጻር ከዚህ በላይ መስራት እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን የገለጹት አምባሳደሩ በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት ስምንት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ እና በውጭ ሀገራት ከሚገኙ ኤምባሲዎች እና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ጋር በመሆን ዳያስፖራው በህጋዊ መንገድ እንዲልኩ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም አመልክተዋል።
ዳያስፖራው በባንክ ስርዓት ሬሚታንስ መላኩ ገንዘቡ አስተማማኝነት እንዲኖረውና አጭበርባሪዎች እጅ እንዳይወድቅ የሚያደርግ መሆኑ ትልቅ ጠቃሜታ እንዳለው ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት።
ለሬሚታንስ መላኪያ ተብሎ ዳያስፖራው ይከፍለው የነበረውን ክፍያ ባንኮች በመሸፈን ማበረታቻ እያደረጉ እንደሆነ ገልጸው ዳያስፖራው ዋስትና የሚሰጠውን ህጋዊ የመላኪያ አማራጭ እንዲጠቀም ጥሪ አቅርበዋል።
ዳያስፓራው https://www.unite.et/ በተሰኘው አማራጭ በመንግስት እና የግል ባንኮች የውጭ ምንዛሬ ሂሳብ ቁጥር በመክፈት ገንዘብ ማስተላለፍ መጀመሩ አካውንት ለመክፈት የነበረውን የወረቀት አሰራር በማስቀረት ትልቅ ለውጥ ማምጣቱን ጠቁመዋል።
አምባሳደር ፍጹም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከህገ ወጥ የገንዘብ አዘዋዋሪዎች እንዲጠበቁ ያወጣውን ማሳሰቢያ ተከትሎም ከሚሲዮኖች ጋር በመሆን ለዳያስፖራው ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።
በህገ-ወጥ መንገድ በሚደረግ የገንዘብ ማስተላለፍ ድርጊት ላይ የሚሳተፉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በማሳሰብ ዳያስፖራው በህጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ቤት ገንዘብ በመላክ የኢትዮጵያን ልማት እና እድገት በአዎንታዊ መልኩ እንዲደግፍ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።