በ19 ጨዋታ 50 ግብ ያስቆጠረው የቅዱስ ጊዮርጊሱ ታዳጊ

You are currently viewing በ19 ጨዋታ 50 ግብ ያስቆጠረው የቅዱስ ጊዮርጊሱ ታዳጊ

AMN – ነሐሴ 8/2017 ዓ.ም

ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ተስፋ የጣለበትን ታዳጊ አግኝቷል፡፡

እንየው ስለሺ ይባላል፤ ከአርባምንጭ የፓይለት ፕሮጀክት ተመልምሎ የቅዱስ ጊዮርጊስን ከ17 ዓመት በታች ቡድን ተቀላቅሏል፡፡

በ2017 የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ባዘጋጀው የእድሜ ምርመራ (MRI) ያለው ከ17 ዓመት በታች ውድድር ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው እንየው የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኗል ፡፡

ግቦችን እያዘነበ የተጋጣሚ ተከላካዮችን ፋታ የሚነሳው ተጫዋቹ፣ እራሱን በደንብ ያጎለበተው በአርባምንጭ ነው፡፡

በፓይለት ፕሮጀክት ሦስት ዓመት ተጫውቶ ሁለቱን በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እንዳጠናቀቀ የሚናገረው የፈረሰኞቹ ተስፋ፣ ለእድገቱ ትልቅ ሚና የተጫወቱት አሰልጣኞቹ እንደሆኑ ገልጿል፡፡

አዲስ አበባ መጥቶ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከተቀላቀለ በኋላ ይበልጥ የጎለበተው እንየው ስለሺ፣ በዘንድሮው ውድድር በ19 ጨዋታ 50 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል፡፡

የግቦቹ መጠን በሀገራችን በየትኛውም እርከን የተለመደ አይደለም፡፡

እንየው ለዚህ የበቃሁት በቡድን አጋሮቼ እገዛ ነው ይላል፡፡

’’የቡድን አጋሮቼ ባያግዙኝ እዚህ ደረጃ አልደርስም የሚለው ተጫዋቹ፣ ጓደኞቼ ምስጋና ይገባቸዋል በእነርሱ ጥረት ጭምር ነው ጎልቼ የወጣሁት፡፡’’ ሲል ተናግሯል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ከ17 ዓመት በታች ዋና አሰልጣኝ ዮናስ እስክንድር፣ እንየው የሚጫወትበትን ቦታ መቀየሩ የበለጠ ግብ አስቆጣሪ እንዲሆን እንደረዳው ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል፡፡

’’አርባምንጭ እያለ ብዙ ጊዜ በቀኝ መስመር አጥቂነት ተጫውቷል፤ ብቃቱን ተመልክቼ የዘጠኝ ቁጥር ቦታ እንዲጫወት ሳደርገው በመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች ላይ ግብ አላስቆጠረም ነበር፤ ቦታውን ሲላመድ ግን በርካታ ግቦችን አስቆጥሮልናል’’ ሲል አሰልጣኙ ተናግሯል ፡፡

እንደ አሰልጣኝ ዮናስ እስክንድር እንየው ያስቆጠራቸው ግቦች ብዛት በቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ ታሪክ ናቸው፡፡

’’በዓመት 50 ግብ ያስቆጠረ የለም፤ ከዚህ ቀደም እንዳነበብኩት ጋሽ ይድነቃቸው ተሰማ 48 ግብ አስቆጥረው ያውቃሉ’’ በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡

እንየው ስለሺ በቡድን አጋሮቹ የሚወደድ ተጫዋች ነው፤ ብቃቱ ፣ ታታሪነቱ እና ለግብ ያለው ርሃብ በቡድን አጋሮቹ ዘንድ ከበሬታ እንዲሰጠው አድርጎታል፡፡

የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ያዘጋጀው ከ17 ዓመት በታች ውድድር የፊታችን ቅዳሜ ይጠናቀቃል፡፡

ትልቁ ምኞቴ ከሀገር ውጪ በከፍተኛ ደረጃ መጫወት ነው የሚለው እንየውም፣ በዓመቱ ያስቆጠራቸውን የግብ ብዛቶች ከ50 በላይ ለማድረግ ተዘጋጅቷል፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review