AMN- ነሐሴ 8/2017 ዓ.ም
የሰው ልጅ እንደተወለደበት እና እንዳደገበት አካባቢ ነገሮችን የመላመድ እና የመረዳት ተፈጥሮ አለው፡፡ ይህ ማለት ግን ስለተወለደበት እና ስላደገበት ብቻ ተፈጥሮን ይላመዳል ማለት አይደለም፡፡
የሚያጋጥሙትን ነገሮች በመቋቋምና ሰው ሰራሽ መፍትሄ በመስጠት ራሱን ሊያላመድ ይችላል፡፡ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ራሱን አሰናኝቶ ይኖራል እንጂ ተፈጥሮን መቀየር ግን አይችልም፡፡
ተፈጥሮ ከለገሰችን ስጦታዎች አንዱ ወቅቶች ናቸው፤ እነዚህ ወቅቶች የስራ ባህላችን፣ አኗኗራችን፣ ማህበራዊ መስተጋብራችን እና ባህሪያችን ላይ የሚያሳድሩት አዎንታዊና አሉታዊ ክስተቶች አሉ፡፡
ወቅቱም ክረምት እንደመሆኑ፣ ክረምትና ሌሎች ወቅቶች ከሰው ልጅ ስነ-ልቦና ጋር ያላቸው ግንኙነትን በተመለከተ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ሚዲያ ጋር ቆይታ ያደረጉት የስነ-ልቦና ባለሞያ ዶክተር ሰላም አባዲ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡ እንደ ዶክተር ሰላም አባዲ ገለፃ፣ የሰው ልጅ ከተኛበት ሲነሳ በሚያየው የፀሃይ ብርሃን የደስታና የተነሳሽነት ስሜት ይፈጥራል፡፡
በተቃራኒው በክረምት ወይንም ደመናና ዝናባማ በሚሆንበት ጊዜ ከአልጋችን በቶሎ ያለመውረድ እና ለመነሳት ያለመፈለግ ስሜቶች ይፈጠራሉ፣ ይህም ከስነ-ልቦና ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው ይላሉ ዶክተር ሰላም፡: ከዚህ በመነሳት በአየር ፀባይ ምክኒያት አዕምሯችን ከኛ ሁኔታ(ሙድ) ጋር የሚያራምዳቸውን ጉዳዮች በሶስት በመክፈል ዶክተር ሰላም ሙያዊ አስተያየታቸውን ያስቀምጣሉ፤ የመጀመሪያው ፀሃይ ሲወጣ አዕምሯችን ውስጥ የሚፈጠር ወይንም የሚመነጭ ሴሪቶኒ የተባለ ንጥረ ነገር አለ፡፡
ይህ ንጥረ ነገር ሰውነታችን የተሻለ ስሜት እንዲኖረው ጉልበት እና ጠንካራ ሃይል እንድናገኝ ትኩረት እንዲኖረን የሚያደርግ ሲሆን፣ በዚህ ምክኒያትም የተሻለ መነሳሳት በመፍጠር ከሰዎች ጋር ያለን ቅርርብ እና ቁርኝት እንዲጨምር አዳዲስ ነገሮችን እንድንጀምር ይረዳናል በማለት ያብራራሉ፡፡
በተቃራኒው የፀሃይ ብርሃን በማይይኖርበት ወቅት፣ የተነሳሽነት ስሜት አለመኖር፣ ድብርት መፈጠር እና ድብርት ውስጥ እንድንቆይ የሚያደርግን ሁኔታ እንደሚፈጠርም ነው ዶክተር ሰላም የሚገልጹት፡፡
በሁለተኛነት፣ ክረምትን የድብርት ወቅት አድርጎ ማሰብ አለ፤ ይህ ደግሞ የሁሉም ሰው እውነታ አይደለም፤ ይልቁን ለአንዳንድ ሰዎች ድብርት እንደሚያጭር ሁሉ ለሌሎች ደግሞ የመረጋጋት ስሜትን በመፍጠር በፅሞና እንድናስብ እና እንድናሰላስል ነገሮች ላይ ትኩረት በማድረግ ውስጣችንን እንድንመለከት ያደርጋል፡፡
ወደ ውጭ የምናደርገውን ዕይታ ወደ ራሳችን እንድናይ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን እና ወቅቶች ይዘውት የሚመጡት መልካም አጋጣሚ መኖሩን ያነሳሉ፡፡
ይሁን እንጂ በክረምት ወቅት እንደ መብረቅ ነጎድጓድ እና ዶፍ ዝናብ በሚከሰትበት ሰአት በስነ-ልቦና ላይ የፍራቻና የመረበሽ እንዲሁም የመደናገጥ ስሜት መፍጠሩ ደግሞ ከተፈጥሮ ጋር የሚያያዝ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡
በሶስተኛነት፣ በየወቅቱ የሚፈጠር የሙቀት መጠን ከሰው ልጆች ስነ-ልቦና ጋር ቀጥታ ግንኙነት አለው ይላሉ፡፡
ለማሳያ ያክል ከመጠን ያለፈ ሙቀትን እና ወበቅ በክረምትም ሆነ በሌሎች ወቅት ሲፈጠር ለአይምሯችን ጤና ምቾት የማይሰጥ እና ነገሮች ላይ ትኩረት አድርጎ ስራን ለመከወን አለመቻል የመነጫነጭ እና ትዕግስት የማጣት ሁኔታዎች ይከሰታሉ፡፡
እንዲሁም አየር ፀባዩ ቀዝቃዛ እና የተረጋጋ ሲሆን፣ ትኩረታችን ይጨምራል ለስራ ትኩረት መስጠትና የምንሰራው ስራ መጨመር እንደሚስተዋል ዶክተር ሰላም አውግተውናል፡፡
በመጨረሻም የሰው ልጅ የአየር ፀባይ ሁኔታ ራሱን በማላመድ ከድብርት እና ሊያጋጥሙ ከሚችሉ ችግሮች ለመውጣት ወቅቱን ያማከለ የአዕምሮ ዝግጅት በማድረግ አኗኗሩን በማስተካከል ከሚፈጠሩ የስነ-ልቦና ጫና መላቀቅ እንደሚችል ነው ዶክተር ሰላም አባዲ ሃሳባቸውን ያጋሩን፡፡
ውድ ተከታዮቻችን ከክረምት ጋር ተያይዞ የሚፈጠርባችሁ ስሜትና በወቅቶች ላይ ያላችሁ ምልከታ ምን ይመስላል ? ሃሳባችሁን አጋሩን፡፡
በያለው ጌታነህ