ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ ያገኘችውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከብራዚል ጋር ያላትን የኢኮኖሚ እና ንግድ ትብብር ለማጠናከር እየሰራች እንደምትገኝ በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ ገለጹ።
የኢትዮ-ብራዚል የቢዝነስና የቱሪዝም ፎረም መስከረም 16 እስከ 18 ቀን 2018 ዓ.ም በሳኦ ፓውሎ ይካሄዳል።
በፎረሙ ላይ ከሁለቱ ሀገራት የተወጣጡ በርካታ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ፥ ፎረሙ ኢትዮጵያ እና ብራዚል በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ቱሪዝም እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚያስችል ለኢዜአ ገልጸዋል።
ፎረሙ ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትስስር ለማሳደግ እያከናወነች ያለውን ስራ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በብሪክስ አባልነቷ የደቡብ ደቡብ ትብብር እንዲጠናከር እያደረገች ያለውን ጥረት ከመደገፍ አኳያም የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት አመልክተዋል።
በመንግስት ቁልፍ ተብለው በተለዩት የግብርና፣ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ቱሪዝም እና የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ ዘርፎች) የተሰማሩ የብራዚል ባለሀብቶች እና ኩባንያዎች በፎረሙ ላይ እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በፎረሙ ላይ በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ አማካኝነት የተፈጠሩ ምቹ የንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና ቱሪዝም እድሎችን እንደምታስተዋውቅ ነው አምባሳደሩ የጠቆሙት።
የመንግስት እና የንግድ እንዲሁም የንግድ-ለንግድን ጨምሮ ሌሎች የሁለትዮሽ ውይይቶች እንደሚደረጉ አመልክተዋል።
የሀገራቱን የባህል ትብብር የሚያጠናክር ሁነት እንደሚካሄድም እንዲሁ።
ከዚህ ቀደም የተደረጉ የሀገራቱ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ፎረሞች የኢኮኖሚ ትብብርን እንዲጠናከር መልካም አጋጣሚ መፍጠራቸውንና የብራዚል ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝቶችን እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
የባለሀብቶቹን ፍላጎት ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ውጤት ለመቀየር በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ በሰኔ ወር 2017 ዓ.ም በብራዚል ሪዮ ዴጄኔሮ በተካሄደው 17ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ መሳተፉ አይዘነጋም።