የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በዲጂታል ኢቢሲ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ በሁለንተናዊ የልማት ሥራወች ስኬት በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ በከተማ እና የገጠር ኮሪደር ልማት አዲስ ምዕራፍ ከፍታለች ያሉት ሚኒስትሩ፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት ዓለም አቀፋዊ ተፅእኖ መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ መገንባቱን ገልጸዋል።
በማኅበራዊ ዘርፍም የሰለጠነ የሰው ኃይል እና በበጎነት መርሕ የሚመራ መልካም ዜጋ በማፍራት ረገድ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል ።
በሜጋ ፕሮጀክቶች ረገድ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከፍጻሜው ጫፍ መድረሱንም ነው ያነሱት።
አክለውም የባሕር በር ተጠቃሚነትን በሚመለከት የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ጉዞ ከግማሽ መንገድ በላይ መራመዱን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ በሁሉም እንቅስቃሴዎች እያገኘች ያለውን ጉልህ ስፍራ ለማስተጓጐል፤ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ከሚዘውሯቸው የውስጥ ባንዳዎች ጋር በመተባበር ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ፈተና ተከፍቷል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ገፅታ ለማጠልሸት የሚደረገውን እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን በዲጂታል ምህዳር በመተባበር የመመከት ሥራ እንደሚጠበቅባቸውም ሚኒስትሩ ማመላከታቸዉን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
ግጭት እና ብጥብጥን የኢትዮጵያ ማዳከሚያ ስልት አድርገው የሚጠቀሙ ኃይሎችን አላማ በመረዳት፤ ዜጎች የሀገርን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ በጋራ እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል።