ሩሲያ በቅርቡ የጀመረችውን የበይነ መረብ ቁጥጥር ለማጠናከር የሚያስችል ገደብ በመልእክት መላላኪያ መተግበሪያዎቹ ዋትስ አፕ እና ቴሌግራም ላይ ማስቀመጧን አስታውቃለች።
ገደቡ መተግበሪያዎቹን በመጠቀም የድምፅ እና ቪዲዮ ጥሪ ማድረግን የሚከለክል ነው።
የሀገሪቱ የሚዲያ እና በይነ መረብ ቁጥጥር ባለስልጣናት፣ ውሳኔው ወንጀልን ለመከላከል እና ብሔራዊ ደህንነትን ለማስጠበቅ ታስቦ የተላለፈ መሆኑን አስታውቀዋል።
ገደቡ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጠቃሚች ላይ ተፅዕኖ እንደሚያደርግ አልጀዚራ ዘግቧል።
እንደ ህግ አስከባሪ ኤጀንሲዎች እና ይግባኝ ጠያቂ ዜጎች ከሆነ፤ ቴሌግራም እና ዋትስ አፕ በሩሲያ ለተለያዩ የማጭበርበር እና ሌሎች ወንጀሎች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።
ሞስኮ፣ የበይነ መረብ አገልግሎት ሰጪዎቹ በሕግ አስከባሪዎች በሚጠየቁበት ጊዜ የተጠቃሚዎችን መረጃ ማቅረብ እንዲችሉ ትፈልጋለች ብለዋል።
ገደቡም መተግበሪያዎቹ የሩሲያን የተጠቃሚዎችን መረጃ የማግኘት ጥያቄ እስካልመለሱ ድረስ የሚቆይ ይሆናል።
ዋትስ አፕ እና ቴሌግራም ተጠቃሚዎች መተግበሪያዎቹን አለአግባብ እንዳይጠቀሙ ጥብቅ ቁጥጥር የሚያደርጉ መሆኑን እና ጎጂ ይዘቶችን በመከታተል እንደሚያስወግዱ ገልፀዋል።
ሩሲያም አማራጭ ያለችውን ‘ማክስ’ የተሰኘ የራሷን መልእክት መላላኪያ መተግበሪያ ይፋ ብታደርግም የግል ሚስጥርን ከመጠበቅ ጋር የተያያዘ ጥያቄ ማስከተሉን ዘገባው አመላክቷል።
በሊያት ካሳሁን