የወንዝ ዳርቻ ልማት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል

You are currently viewing የወንዝ ዳርቻ ልማት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል

AMN – ነሀሴ 08/2017 ዓ.ም

የአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ በርካታ ወንዞች የተቸሯት፣ ውብና ማራኪ የሆነ መልካምድራዊ አቀማመጥ ያላት ከተማ እንደሆነች ብዙዎች ይመሰክሩላታል፡፡

አዲስ አበባን በሰሜን ምዕራብ በኩል ግማሽ አካሏን አካሎ ቁልቁል የሚመለከታት የእንጦጦ ተራራ ውበትን ከማላበስ ባለፈ በርካታ ወንዞችን ከጉያው አፍልቆ ለግሷታል፡፡

ሆኖም ግን እነዚህ ወንዞች የመዲናዋ ነዋሪዎች ውሃ ሲጠማቸው ጠጥተው የሚረኩባቸው፣ ዋኝተው የሚደሰቱባቸው፣ የቆሸሹ ልብሶችን አጥበው የሚደምቁባቸው፣ በአካባቢያቸው ከሚገኙ ዕፅዋት የሚለገስን ንጹህ አየር ተቀብለው አእምሯቸውን የሚያድሱባቸው ብቻ አልነበሩም፡፡

ወንዞቹ በአግባቡ ካለመያዛቸው የተነሳ ለከፍተኛ ብክለት ተዳርገው ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህ ወንዞች የሚወጣዉ ጥሩ ያልሆነ ሽታ ደግሞ ነዋሪዎችን ለመተንፈሻ አካላት እና ለሌሎችም ተጓዳኝ በሽታዎች ሲያጋልጧቸው መቆየታቸዉ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነዉ፡፡

ይሁን እንጂ በመዲናዋ ከቅርብ አመታት ወዲህ እየተተገበሩ የሚገኙት የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች የአዲስ አበባን ገጽታ ብቻ ሳይሆን ከወንዞች ሲወጣ የነበረዉን መጥፎ ሽታም ቀይሮታል፡፡

በተለይ የወንዝ ዳርቻ ልማቱ ከአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ጋር በተቀናጀ መንገድ ተግባራዊ መደረጉ የከተማዋን የአረንጓዴ ሽፋን ትርጉም ባለዉ መንገድ አሳድጎታል፡፡

የወንዝ ዳርቻ ልማቱ፣ በመዲናዋ የሚገኙ ወንዞችን ከብክለት ከመታደጉም ባለፈ የተስተካከለ የስነ ምህዳር ሚዛን እንዲኖር፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን የሚከላከል እና ምቹ የመኖሪያ አካባቢ እንዲፈጠር አይነተኛ ሚና ተጫዉቷል፡፡

በመዲናዋ የወንዝ ዳርቻ ልማት ከሚከናወንባቸው አካባቢዎች መካከል የቀበና ወንዝ ተጠቃሽ ነዉ፡፡

ወንዙ ከዚህ በፊት በከፍተኛ ሁኔታ ተበክሎ በአካባቢው ነዋሪዎች እና በመዲናዋ የመልካም ገጽታ ላይ ችግር ሲያስከትል እንደቆየ እና አሁን ላይ የወንዝ ዳርቻ ልማት በተካሄደበት የወንዙ ክፍል፣ ስነ ምህዳሩ ተስተላክሎ ለሰው ልጆች ምቹ የመኖሪያ አካባቢ መሆን እንደጀመረ በአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የፕሮጀክት ስራ አስተባባሪ አቶ አማኑኤል ሽብሩ ተናግረዋል፡፡

የልማት ስራ በተከናወነበት የወንዙ ክፍል፣ ከዚህ በፊት የነበረውን ብክለት እና ሽታ ያሰወገደ፣ ለሰው ልጆች ጥሩ በዓዛን የሚለግሱ የተለያዩ የዕፅዋት ዝርያዎች፣ ለመድሃኒትነት የሚገለግሉ ተክሎች፣ የአፈርና ጥበቃ ዕፅዋቶች እንዲሁም ለምግብነት የሚያገለግሉ የጓሮ አትክልቶች መተከላቸውን አቶ አማኑኤል ገልጸዋል፡፡

ወንዙ ከብክለት ነፃ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎችም ልብስ እና ሰውነታቸውን መታጠብ፣ ለተለያዩ አገልግሎት የሚውል ውሃ መቅዳት እንዲሁም ልጆችም ውሃ እየዋኙ መዝናናት መጀመራቸውንም አስተባባሪው አክለው ተናግረዋል፡፡

ሌላው በወንዙ ዳርቻ አካባቢዎች የተሰራው የኮሪደር ልማት በመዲናዋ ለሚኖሩ ነዋሪዎችም ሆነ በታችኛው የተፋሰሱ አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎች ከጎርፍ አደጋ ስጋት እንደሚከላከልም ተመላክቷል፡፡

አብዛኛዎቹ የአዲስ አበባ ወንዞች መዳረሻቸው የአዋሽ ወንዝ ተፋሰስ አካባቢዎች በመሆናቸው፣ በእነዚህ አካባቢዎች በሚኖሩ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ይደርስባቸው ነበር፡፡

አሁን ላይ ከተበከሉ የአዲስ አበባ ወንዞች ወደ አካባቢው የሚሄደው ቆሻሻ እና ጎርፍ በእጅጉ ስለሚቀንስ በአካባቢው የሚከሰተው የጤና እና የጉርፍ አደጋም እንደሚቀንስም ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

በጎርፍ አማካኝነት በብዛት ተግዘው በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ የሚጣሉት የፕላስቲክ ተረፈ ምርቶች በእርሻ ስራ ላይ የሚያሳድሩት አሉታዊ ተፅዕኖም እንደሚቀረፍ ነው የሚገለጸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የወንዝ ዳርቻ የልማት ስራዎች ሲጠናቀቁ የአካባቢን ስነ ምህዳር ከማስተካከል ባሻገር፣ ለመዲናዋ ነዋሪዎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን በማስገኘት የኑሮ ደረጃቸውን ከፍ ያደርጋል፡፡

በመዲናዋ የተጀመረው የአረንዴ አሽራ መርሃ ግብር አዲስ አበባ ከተማን ዘመናዊ ውበትና ገጽታ ከማላበሱ በተጨማሪ ተወዳዳሪ እና የቱሪስት መዳረሻ ከተማ እንድትሆን አስችሏታል፡፡

በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ከመፍጠራቸዉ፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ከመደገፋቸዉ ባሻገር ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለችዉን የአረንጓዴ ልማት ከማሳካት ረገድ የሚኖረዉ ጠቀሜታ የላቀ ነዉ፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review