የሉዓላዊነት ምልክት የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያለልዩነት መደገፍ አለብን ሲል የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ጥሪ አቅርቧል፡፡
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን አስመልክቶ ባወጣዉ መግለጫ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሉዓላዊነትና የእድገት ምልክት በመሆኑ መላው ኢትዮጵያውያን ያለልዩነት ድጋፋቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ የመጠቀም መብቷ ለድርድር እንደማይቀርብ የገለጸዉ ፓርቲዉ ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን በፍትሃዊነት የመጠቀም ሉዓላዊ መብት እንዳላት አስታዉቋል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ህዳሴ ግድብ ባሉ ፕሮጀክቶች አማካኝነት የምታከናውናቸው የኢነርጂ፣ የግብርና ማዘመንና የኢንዱስትሪ ልማት ስራዎች ህጋዊ ብቻ ሳይሆን ለሀገራዊ እድገትና ቀጣናዊ መረጋጋት አስፈላጊ መሆናቸውን ነው ያስታወቀው፡፡
ግብጽ በዓባይ ውሃ ላይ በምታራምደው ጊዜው ያለፈበት፣ መሰረት የሌለውና ኢፍትሃዊ በሆነ ፍላጎት ምክንያት ኢትዮጵያ ከልማት ተከልክላ ልትቆይ አትችልም ሲል ፓርቲው በመግለጫው አስገንዝቧል፡፡
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትከተለው አቋም ፍትሃዊ የጋራ ተጠቃሚነትን በሚደግፉ ዓለም አቀፍ ህጎች ላይ የተመሰረተ መሆኑን የጠቆመው መግለጫው፥ ህዳሴ ግድብ የልዩነት ምንጭ ሳይሆን የተፋሰሱን ሀገራት ህዝቦች የሚያስተሳስር ነው ብሏል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከውስጣዊ የፖለቲካ ልዩነቶች የተሻገረ የልማት፣ የሉዓላዊነት እና የብሄራዊ ደህንነት ጉዳይ በመሆኑ ግድቡን መጠበቅ የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ ኃላፊነት መሆኑንም አስረድቷል፡፡