የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ክረምቱን በንባብ ለሚያሳልፉ ታዲጊዎችና ህጻናት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
ንባብ ለአእምሮ መነቃቃት፣ የማስታወስና የማገናዘብ ችሎታን ለማዳበር፣ ጠንካራና ምክንያታዊ አስተሳሰብን ለመያዝ፣ የሰውን ልጅ ህይወት በሳይንስ ቴክኖሎጂ ለመቀየር የወደፊቱንም ለመተንበይ እንደሚጠቅም የአደባባይ ሀቅ ነው።
ይህንን ቀድመው የተረዱት ታዳጊዎችና ወላጆች በኢንተርኔት ግንኙነት በተሳሰረው ዓለም ሳይዘናጉ፣ የእውቀት አድማስን ከመጽሐፍት ለመሸመትና ትውልዱን ለማነጽ የማህበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ተጽዕኖን ሰብሮ ለማለፍ በአብርሆት ከተመዋል።

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ በአብርሆት ቤተ-መጽሓፍት በመገኘት በቤተ መጽሃፉ ክረምቱን በንባብ እያሳለፉ የሚገኙ ታዳጊዎችን አነጋግሯል፡፡
ታዳጊ ሞኒካ ፍቅሬ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን፣ ከፊልምና ከማህበራዊ ሚዲያ በመራቅ ክረምቱን በአብርሆት ቤተመጽሐፍት በንባብ እያሳለፈች መሆኗን ተናግራለች፡፡
ቤተ-መጽሐፍቱ የተሟላ ግብአትና የተለያዩ መጽሃፎች እንዳሉት የምትናገረው ሞኒካ፣ ከዚህ በፊት የነበረውን መሰረታዊ የመጽሃፍ ችግር መቅረፉንም ገልፃለች፡፡
ታዳጊዎች እውቀታቸውን ለማሳደግ እና ነጋቸውን የተሻለ ለማድረግ የእረፍት ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው ታዳጊ ሞኒካ መልዕክት አስተላልፋለች፡፡

ሌላኛዋ ታዳጊ ሳሮን ጌታቸው በበኩሏ፣ ክረምቱን በንባብ እያሳለፈች መሆኗን ጠቁማ፣ አብርሆት በጽዳት፣ በመጽሐፍት አቅርቦትና በቦታ ስፋት እንዲሁም በቴክኖሎጂ አጠቃቀም የተሻለ መሆኑን ለዝግጅት ክፍላችን አስረድታለች።
አብርሆት፣ የማንበብ ፍላጎታችን እንዲጨምር እና ከቤት ወጥተን ክረምቱን በቤተ መጻሕፍቱ እንድናሳልፍ አድርጓል ብላለች ሳሮን።
በአብርሆት ቤተ መጽሃፍት ውስጥ ያገኘናቸው ዶክተር ስንታየሁ ተስፋ በበኩላቸው፣ አስተማሪም ወላጅም መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ለአብርሆት ቤተ መጽሃፍ መጽሐፍትን በመግዛት በስጦታ መልክ ማበርከታቸውን እና ልጆቻቸውንም ወደ እዚሁ ቤተ መጽሃፍ እያመጡ የንባብ ባህላቸውን እንዲያዳብሩ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ዶክተር ስንታየሁ፣ ሌሎች ወላጆችም በክረምቱ የእረፍት ጊዜ ልጆቻቸውን ወደ አብርሆት ቤተ መጽሃፍት እየላኩ የንባብ ችሎታቸውን እና እውቀታቸውን እንዲያዳብሩ እንዲያደርጉ ይመክራሉ፡፡

በአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ከልጃው ጋር ያገኘናቸው አቶ ግዛቸው ሽፈራው እንዳሉት ደግሞ፣ ከዚህ በፊት በከተማዋ የተሟላ አገልግሎት የሚሰጥ መጽሐፍት ቤት እንዳልነበር አስታውሰው፣ አሁን ላይ አብርሆት ቤተ መጽሃፍት የክረምቱን ጊዜ በአግባቡ በመጠቀም ለቀጣይ የትምህርት ዘመን የእውቀት ስንቅ ለመያዝ የተመቻቸ እድል ፈጥሯል ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ግዛቸው አክለውም፣ ወላጆች በክረምት ልጆች ከትምህርት ርቀው እንዳይቆዩ እና የማንበብ ልምድ እንዲያካብቱ በእረፍት ጊዚያቸው በቤተ መጽሃፍቱ እንዲጠቀሙ ማበረታታት ይችላሉ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በአለኸኝ አዘነ