ትራምፕ ዛሬ ከፑቲን ጋር በአላስካ ከሚያደርጉት ወሳኝ ውይይት አስቀድሞ በነጩ ቤተመንግስት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ላለው ጦርነት ማብቂያ እንደሚያበጁለት እምነታቸውን የገለፁ ሲሆን ይህ ግን ከዩክሬን ጋርም ተጨማሪ ንግግር ማድረግን የሚጠይቅ ነው ብለዋል፡፡
“እንደማስበው ፑቲን ወደ ሰላም ይደርሳሉ፤ ዘለንስኪም ወደ ሰላም ይደርሳሉ” ሲሉ በመገለጫቸው አብራርተዋል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ እና የአውሮፓ አጋሮቹ፤ አሜሪካ እና ሩሲያ የሚያደርጉት ውይይት በቀጣይ በዩክሬን ላይ ጉዳት የማያደርስ መሆኑ ሊረጋገጥ እንደሚገባ አቋም መያዛቸው ይታወቃል፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ ወሳኙ ዛሬ ከሚካሄደው ውይይት በኋላ ያለው 2ኛው ውይይት ነው ሲሉ የተናገሩትም ለዚሁ ይመስላል፡፡
2ኛው ዙር ውይይት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ፣ የሩሲያው ፑቲን፣ እራሳቸው ትራምፕ እና የአውሮፓ መሪዎችም የሚሳተፉበት እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡
የሩሲያው ፕሬዘዳንት ፑቲን በበኩላቸው ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ቀጥሎ በተከሰተው አውዳሚው ግጭት ተሳታፊ የሆኑ አካላትን በማግባባት ጦርነቱን ለማስቆም አሜሪካ የምታደርገው ጥረት ክብር የሚሰጠው ነው ብለዋል፡፡
ትራምፕ እና ፑቲን በዛሬው ውይይታቸው በመካከላቸው ስላለው የኢኮኖሚ ትስስር እንደሚነጋገሩም ከክሬሚሊን የወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡
የአላሳካው ውይይት ፍሬያማ ሳይሆን ቢቀር እና ፑቲን ሰላም ለማምጣት ዳተኛ ሆነው ቢገኙ ግን ሩሲያ ለማዕቀብ ልትጋለጥ ትችላለች ማለታቸውን አር ቲ ኢ ዘግቧል፡፡
በማሬ ቃጦ