AMN – ነሐሴ 9/2017 ዓ.ም
ከክረምት ወደ ፀደይ የመሸጋገሪያ ወርን ጠብቀው የኦሮሞ ቆነጃጅት ልጃገረዶች ወደ ብርሀናማ ወቅት መሸጋገራቸውን የሚያበስሩበት ነው ሺኖዬ።
ልጃገረዶች ፀደይ ወቅቱን ከማብሰራቸው በተጨማሪ ተፈጥሮ በራሷ ግዜ ሺኖዬ መቃረቡን በልምላሜ እና አበባዎችን በማፍካት ትናገራለች።
ልጃገረዶቹም ሼኖዬን ለማክበር ፀጉራቸውን በመሰራት ጌጣጌጣቸውን ማዘጋጀት ቀደም ብለው ሽርጉዱን ይጀምራሉ።

ሺኖዬ ለሳምንት ሲከበር ለምለም ወይም እርጥብ ቄጤማ እና ቁኒ (አበባ) ይዘው በየቀዬው እየዞሩ ከክረምት ጨለማ ወደ ጸደይ ብርሀን መሸጋገራቸውን፤ ደስታቸውን በዜማ ያበስራሉ።
በእዚህ ወቅት ከሴት ልጃገረዶች በተጨማሪ ወጣት ወንድ ጉብሎችም ጎቤ በየአመቱ ከክረምት መውጣታቸውን ወደ ጸደይ መሸጋገራቸውን በዜማ እና በጭፈራ የሚገልፁበት ወቅት ነው።
ጎቤና ሺኖዬም ዓመታዊ የኦሮሞ ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች የዘመን መለወጫ የብሥራት የአደባባይ ጨዋታ ነው።
ይህ የወጣቶችን ባሕላዊ ክዋኔ የሕዝቦችን አንድነትና ፍቅር የሚያጠናክር የዘመን መለወጫ መዳረሻ ባሕላዊ ጨዋታ መሆኑም ይታወቃል፡፡
የመዲናዋ ድምቀቶች የሆኑት እነዚን ባህሎች ለማክበር ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ ይገኛል።

ጎቤ እና ሺኖዬ የአዲስ አበባ ልዩ ውበት እየሆነ መምጣቱን የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ገልጾ፤ የከተማዋ ድምቀትን ለማጉላት ዝግጅት ተጀምሯል።
ጎቤ እና ሺኖዬ የአዲስ አበባ ልዩ ውበት እየሆነ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሁንዴ ከበደ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ተናግረዋል።
ኮሚሽነሩ የጎቤና ሺኖዬ ካርኒቫልን ሥርዓት እና ወግን በጠበቀ መልኩ በአዲስ አበባ ለማክበር ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
በአገሪቱ ውስጥ ባለፉት ዓመታት የመጣው ለውጥ ጎቤና ሺኖዬ ታሪካዊ አሻራውን ጠብቆ እንዲከበር ማስቻሉን አቶ ሁንዴ ገልፀዋል።

ይሄም ለኦሮሞ ህዝብ ትልቅ ትርጉም እንደሚሰጥ የተናገሩት የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽነሩ፣ ጎቤና ሺኖዬ የተሳሳቱ አመለካከቶችን በማስተካከል ከገዳ ስርዓት በመነጨው ባህልና ትውፊት ለወንድም ለሴትም ክብር እንደሚሰጥ ያመላከተ መሆኑን ተናግረዋል።
ጎቤና ሺኖዬ ባህልና ትውፊቱን እንደጠበቀ ማንሰራራቱ የላቀ ትርጉም አለው ያሉት ኮሚሽነሩ ይሄን ዕንቁ የሆነ እሴት ለትውልድ ማስተላለፍ ተገቢ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል።
ክብረ በዓሉ ለአዲስ አበባ የጎብኚዎችን ፍሰት ከመጨመር ባለፈ የከተማውም ገቢ እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክት በመሆኑ ለዚህ ስኬት ኮሚሽኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ ካርኒቫል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ደርጅት እንዲመዘገብ የማስተዋወቅ ተግባር አየተከናወነ ስለመሆኑም ገልፀዋል።

የቦራቲ ፕሮሞሽን ስራ አስኪያጅ ብሩክ ግርማ ጎቤ፤ ወንድ ወጣቶች ከክረምት ወደ ፀደይ ወይም ከጨለማ ወደ ብርሃን መሻገራቸውን በባህላዊ ጭፈራ የሚገልፁበት ሲሆን ይህንኑ ሁነት ልጃገረዶች ሲገልፁት ሺኖዬ እንደሚባል ይናገራሉ። አቶ ብሩክ ጨምረውም የባህሉ አከባበር ሁኔታ ከዓመት ወደ ዓመት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
ጎቤና ሺኖዬ የህዝብ አንድነትን ከማጠናከር እና ሰላምን ከማስፈን ባለፈ በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ደስታ እንደሚፈጥርም ገልፀዋል።
በዚህም ዓመት ባህልና ትውፊቱን በጠበቀ ሁኔታ ለ7ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ እና አካባቢው ለማክበር ቅድመ ዝግጅቱ መጠናቀቁም ተገልጿል።
በደራርቱ ተሬሳ