በአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ለአህጉራዊ እድገት ተስፋ የሚሆን የፓርቲዎች ጥምረትን እውን ለማድረግ ያለመ ውይይት መካሄዱን ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ

You are currently viewing በአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ለአህጉራዊ እድገት ተስፋ የሚሆን የፓርቲዎች ጥምረትን እውን ለማድረግ ያለመ ውይይት መካሄዱን ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ

AMN- ነሐሴ 9/2017 ዓ.ም

በአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ በአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ትብብርን ለማጠናከርና ለአህጉራዊ እድገት ተስፋ የሚሆን የፓርቲዎች ጥምረትን እውን ለማድረግ ያለመ ውይይት መካሄዱን የብልጽግና ፓርቲ ዓለም አቀፍና የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በጋና አክራ “ከፖለቲካ እስከ ብልፅግና” በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደውን 12ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ አስመልክቶ ገለፃ አድርገዋል።

በ12ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ለአህጉራዊ ለውጥ፣ ለዜጎች ተጠቃሚነት እና ለሀገረ መንግሥት ግንባታ በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ መደረሱንም ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገልጸዋል፡፡

በጉባኤው በአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ትብብርን ለማጠናከርና ለአህጉራዊ እድገት ተስፋ የሚሆን የፓርቲዎች ጥምረትን እውን ለማድረግ ያለመ ውይይት መካሄዱን ተናግረዋል፡፡

ጉባኤው የፖለቲካ ፓርቲዎች የዜጎችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ፓርቲዎች ኢኮኖሚያዊ ሽግግርን፣ የዘላቂ ሰላም ግንባታ እና የሀገረ መንግስት ግንባታን ለማረጋገጥ በትኩረት መስራት እንዳለባቸውም መግባባት ላይ መደረሱን ነው ያብራሩት፡፡

ይህም ጠንካራ አፍሪካን ለመገንባት ትልቅ መሠረት የሚጥል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአፍሪካ ፖለቲካን ካለመተማመንና የጥርጣሬ አካሄድ በማውጣት በጋራ አህጉራዊ አጀንዳዎች ላይ አሻራን ለማኖር የሚያስችል ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፤ የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገራዊና አህጉራዊ ሁለንተናዊ ዕድገት ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው መግለጻቸውንም አስታውሰዋል።

ፓርቲዎች በተናጠል ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ባሻገር መተማመን፣ መተባበር እና ለጋራ ዓላማ መግባባት ፈጥረው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸውም መነሳቱን ገልጸዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ለጠንካራ ሀገርና አህጉር ግንባታ፣ ለሀገረ መንግስት ቅቡልነት እና ለተረጋጋና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህል ግንባታ ትልቅ ትኩረት በመስጠት መስራት እንዳለባቸው መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡

ፓርቲዎች ውስጣዊ ሪፎርም በማድረግ ለአዎንታዊ እና ዘላቂ ሰላም ግንባታ አሻራቸውን ማኖር እንዳለባቸውም መግባባት ላይ መደረሱን መጠቆማቸውን ተዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review