የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ ለኡለማዎች ምርጫ ድምፅ ሰጡ።
ፕሬዚዳንቱ በአዳማ ከተማ ሁዳ መስጂድ በመገኘት ድምፅ ከሰጡ በኋላ ባስተላለፉት መልእክት መጂሊሱ ጠንካራ ኢስላማዊ ተቋም ለፍጠርና ህዝበ ሙስሊሙን ለማገልገል እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የዛሬው ምርጫም ይህንኑ አላማ ያደረገ ነው ብለዋል።
በዚህም መሰረት በሀገሪቱ በዛሬው እለት የኡላማዎች ምርጫ የድምፅ አሰጣጥ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
ህዝበ ሙስሊሙ መሪዎቹን በሚመርጥበት በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ በንቃት በመሳተፍ አደራን መወጣት እንደሚገባ አስታውቀው፤ እርሳቸውም በዚሁ መልኩ ድምፅ መስጠታቸውን ተናግረዋል።
የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ጥሩ ዝግጅት የተደረገበት፣ ፍትሃዊና ተአማኒ መሆኑን ገልጸው፤ የዑለማዎች ምርጫው በዚህ ደረጃ እንዲካሄድ የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድና በየደረጃው ያሉ ኮሚቴዎች ላደረጉት ጥረትና ትብብር አመስግነዋል።
በቀጣይ እሁድም የድምፅ አሰጣጡ በወጣቶች፣ ምሁራን፣ ሴቶችና በማህበረሰብ ደረጃ የሚቀጥል በመሆኑ ተሳትፎው ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።