ሀሰተኛ የግዢ ደረሰኝ በማዘጋጀትና በማሰራጨት ወንጀል ላይ የተሰማሩ አስራ ሁለት ተጠርጣሪዎችን በመያዝ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ገለጸ።
በዚህም መንግስት ሊያጣ የነበረውን ከ480 ሚሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉንም አስታውቋል።
ሀሰተኛ የግዢ ደረሰኝ ማዘጋጀት፣ ማሰራጨትና መገልገል ወንጀል የተፈፀመው በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ልዩ ቦታው ፊስቲቫል ህንፃ ሀያ ሁለት ማዞሪያ አካባቢ እና በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ክልል ልዩ ቦታው አብደላ ህንፃ ልህቀት ህንፃ እንዲሁም ጌጃ ሰፈር በሚገኘው ብሌን ፕላዛ ህንፃ ውስጥ ለንግድ ስራ በሚል ቢሮ ተከራይተው ከ2015 እስከ 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑን ፖሊስ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል በላከው መረጃ ጠቁሟል።
ተጠርጣሪዎቹ የተለያዩ የጎዳና ተዳዳሪዎችን እና በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ሰዎችን በመመልመልና በገንዘብ በመደለል ግለሰቦቹ ሀሰተኛ ስም ተጠቅመው የቀበሌ መታወቂያ፣ ዲጂታል ፋይዳ መታወቂያ፣ መንጃ ፈቃድ እና የቁጠባ ሂሳብና የባንክ ደብተር እንዲሁም የውክልና ሰነዶችን አዘጋጅቶ የንግድ ፈቃድ ማውጣታቸው ተመላክቷል፡፡
በዚህም ከተለያዩ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ አቅራቢ ድርጅቶች ጋር የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ በማውጣት፣ የእጅ በእጅ የሽያጭ ደረሰኝ በማሳተም፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገቢዎች ቢሮ ልደታ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሚል ሀሰተኛ ክብ ማህተም እና በዚሁ መስሪያ ቤት የሚታወቅ የመረጃ ኦፊሰር ስም የያዘ ቲተር በማዘጋጀት ሀሰተኛ ደረሰኞችን ለተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች እያዘጋጁ ሲያሰራጩ እንደነበር ፖሊስ ገልጿል።
ፖሊስም በተጠርጣሪዎቹ ላይ መረጃን መሠረት ያደረገ ተከታታይነት ያለው ጥናትና የክትትል ስራ በመስራት በወንጀሉ የተሳተፉ አስራ ሁለት ግለሰቦችን ይዞ ምርመራ እያጣራባቸው እንደሚገኝም የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የሙስና ገቢዎችና ሸማቾች ወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት ገልጿል።