በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ እና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች የአዋሽ ወንዝ ሙላት ባስከተለው ጎርፍ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች በተለያዩ አካላት እየተደረገ ያለው ድጋፍ አበረታች መሆኑን የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሰአዳ አብዱራህማን ገለጹ።
ጨፌ ኦሮሚያ በአዋሽ ወንዝ ሙላት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ አድርጓል።
አፈ ጉባኤዋ በዞኖቹ በወንዙ ሙላት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል።
ተጎጂዎችን በጊዜያዊነት ለመደገፍ የተለያዩ አካላት እያደረጉ ያሉት ድጋፍ የሚበረታታ ነው ሲሉም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በእስካሁኑ ሂደት በቡሳ ጓኖፋ አማካኝነት ለተፈናቃዮቹ እየተደረገላቸው ያለው የእለት ደራሽ እርዳታ በበጎ መልኩ የሚታይ መሆኑን ያወሱት አፈ ጉባኤዋ፤ አሁንም የተለያዩ አካላት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናከሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኦሮሚያ ክልል ቡሳ ጎኖፋ ኃላፊ አቶ መሃመድ ጁንዳ በበኩላቸው፣ በአዋሽ ወንዝ ሙላት ምክንያት ከሁለቱ ዞኖች የተፈናቀሉ ወገኖችን በራስ አቅም ለማገዝ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።
ቡሳ ጎኖፋ የመደጋገፍ ባሕልን የሚያጠናክር ስርዓት በመሆኑ ሕብረተሰቡም በቡሳ ጎኖፋ አማካኝነት የተጎዱ ወገኖችን እያገዘ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ ቡሳ ጎኖፋ አማካኝነት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ጠቅሰው፤ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ተጎጂዎችን ለማገዝ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።