የፋብሪካው የምርት ውጤት

You are currently viewing የፋብሪካው የምርት ውጤት

“ለማኑፋክቸሪንግ የወጪ ንግድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው”

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የቶዮ የፀሐይ ብርሃን ኃይል ማመንጫ ፋብሪካን ጎብኝተዋል

በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የቶዮ የፀሐይ ብርሃን ኃይል ማመንጫ ፋብሪካ በከፍተኛ ጥራት የሚያመርታቸው የፀሐይ ብርሃን ሀይል ማመንጫዎች በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚገኘውን የወጪ ንግድ በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናትናው ዕለት በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የፀሐይ ብርሃን የኃይል ማመንጪያዎችን በማምረት ላይ ያለውን የቶዮ የፀሐይ ብርሃን ኃይል ማመንጫ ፋብሪካን እንቅስቃሴ በጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ፋብሪካው በከፍተኛ ጥራት በብዛት ምርት የማምረት አቅም የተላበሰና በዘመናዊ የማሽን ሥርዓት የሚሰራ ነው፡፡

ሁለት ተጨማሪ ማምረቻዎች በግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኙና ወደ ምርት የገባውን ማምረቻ ሥራ ሂደት መመልከታቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ ™ሥራው እሴት የተጨመረባቸው እና ያስቀመጥናቸውን ግቦች እና ፖሊሲዎች የሚያሳኩ ጨዋታ ቀያሪ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ከሚያደርገው የኢንቨስትመንት ስትራቴጂያችን ጋር የተጣጣመ ነው∫ ብለዋል፤ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መረጃ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና ልዑካቸው ጋር በመሆን ከሶስት ወር በፊት በቬትናም ለሶስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው በሀገሪቱ የፀሐይ ብርሃን ሐይል ማመንጫዎችን (ሶላር ፓኔል) በማምረት ወደ ውጭ የሚልከውን ቶዮ የተሰኘውን የጃፓን ኩባንያ ተመልክተዋል፡፡ ኩባንያው በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመግባት ስራ የጀመረ ሲሆን፣ በጉብኝታቸው ፋብሪካው የፀሐይ ብርሃን ሀይል ማመንጫዎችን ከማስፋት በተጨማሪ የፀሀይ ሀይል ማመንጫዎች ግንባታ ላይ እንዲሳተፍ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በጉብኝታቸው ወቅት ባደረጉት ንግግር በእስያ በወጪ ንግድ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ሀገራት መካከል ቬትናም አንዷ ናት፡፡ በዓመትም እስከ 400 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ከወጪ ንግድ ታገኛለች፡፡ የውጭ ንግዷንም ያሳደገችው ኢንቨስትመንትን በመሳብ ነው፡፡ ከዚህም ኢትዮጵያ ልምድ በመቅሰም የወጪ ንግድ አቅሟን ማሳደግ ይጠበቅባታል፡፡

ቬትናም ከወጪ ንግድ ከፍተኛ ገቢ ከምታገኝባቸው ዘርፎች አንዱ የፀሐይ ብርሃን ሀይል ማመንጫ እንደሆነ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ የምትከተለው የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲ እንደመሆኑ አዳጊ የሆነውን የሀይል አቅርቦት ፍላጎቷን ለመመለስ ንፁህ የሀይል አማራጮች ላይ መስራት ያስፈልጋታል፡፡ ለዚህም ከፍተኛ የማምረት አቅም ያለው የቶዮ የፀሐይ ብርሃን ኃይል ማመንጫ በኢትዮጵያ ያለውን ተሳትፎን እንዲያጠናክር  መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቬትናም የቬትናም ጠቅላይ ሚኒስትር ፋም ሚን ቺን በቤተ መንግሥታቸው ይፋዊ የአቀባበል ስነ ስርዓት ያደረጉላቸው ሲሆን፣ ሁለቱ መሪዎችና የልኡካን ቡድኖቻቸው ለትብብር የሚሆኑ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በተለይም የልምድ ልውውጥንና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ መለዋወጣቸው ይታወሳል፡፡

መሪዎቹ በተገኙበትም ሁለቱ ሀገራት በንግድ እና በትምህርት  ትብብር ላይ የመግባቢያ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል፡፡  በተጨማሪም በአዲስ አበባ እና በሃኖይ መካከል በኢትዮጵያ አየር መንገድ የቀጥታ በረራ መንገድ የሚያመቻች የሲቪል አቪዬሽን ስምምነት ተደርጓል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቬትናም ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከተመሰረተ ከሃምሳ አመታት በኋላ በሀገር መሪ ደረጃ የመጀመሪያ ይፋዊ ጉብኝት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review