መዲናዋ እና ኮንፈረንስ ቱሪዝምየተወዳጁበት ምስጢር

You are currently viewing መዲናዋ እና ኮንፈረንስ ቱሪዝምየተወዳጁበት ምስጢር

ከተሞችን ለጉባኤ አስተናጋጅነት ከሚያስመርጣቸው መካከል ምቹ መሰረተ ልማት አንዱ እንደሆነ ተገልጿል

“በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ርዕይ ያለው አመራር አስገራሚ ለውጥ እያስመዘገበች ወደምትገኘው አዲስ አበባ በመምጣቴ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ለውጡ በዓመታት ውስጥ የመጣ ቢሆን ያን ያህል የሚደንቅ ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በአዲስ አበባ በየሰዓቱ፣ በየቀኑና በየሳምንቱ በሚታይ መልኩ ለውጥ እየመጣ ነው፡፡”

ይህ ናይጀሪያዊው፤ ተሰናባቹ የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አኪንውማ አዴሲና (ዶ/ር) ሰሞኑን በቢሾፍቱ አቅራቢያ ለሚገነባው አዲስ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የግንባታ ወጪ ድጋፍ ለማስተባበር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ስምምነት ባደረጉበት ወቅት ያደረጉት ንግግር ነው፡፡

በርግጥም አዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሁለተንተናዊ መልኩ ለውጥ እያመጣች ትገኛለች። እንደ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷም የዓለምን ዓይንና ቀልብ የሳቡ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በስፋት በማስተናገድ ላይ ናት፡፡ በየጊዜው በሚደረጉ ትላልቅ ጉባኤዎች የሚሳተፉ እንግዶችንም እንደ ስሟ ውብና አበባ ሆና፣ እንደ ብርሃን ፈክታ ተቀብላ እየሸኘች ነው፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የከተማዋን የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም በአዲስ አበባ ምክር ቤት ተገኝተው ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ በበጀት ዓመቱ ከ150 በላይ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ኮንፈረንሶች፣ ኤግዚቢሽኖችና ኤክስፖዎች በመዲናዋ  ተካሂደዋል፡፡ በቅርቡም ከሐምሌ 20 እስከ ሐምሌ 22 ቀን 2017 ዓ.ም ለሶስት ቀናት የቆየውን እና የተለያዩ ሀገራት መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የተሳተፉበትን ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት የምግብ ስርዓት ጉባኤ ማካሄዷ ይታወሳል፡፡

ከጷጉሜ 3 እስከ ጷጉሜ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ደግሞ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመተባበር ታስተናግዳለች፡፡ በጉባኤውም ከ20 ሺህ እስከ 25 ሺህ ሰዎች የሚሳተፉ ሲሆን የ45 የአፍሪካ ሀገራትና የሌሎችም ሀገራት መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሊቀ መናብርት፣ ዲፕሎማቶች፣ አምባሳደሮች፣ በዘርፉ የተሰማሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ ሲቪል ማህበራት፣ የልማት አጋሮችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉ የኢፌዴሪ ፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስዩም መኮንን ከአንድ ሳምንት በፊት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል፡፡

አዲስ አበባ እንዴት ተመራጭ ልትሆን ቻለች?

የኢትዮጵያውያንና የአፍሪካ መዲና፣ የተለያዩ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች፣ የበርካታ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች መገኛ የሆነችው አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ ከሚባሉት የዲፕሎማሲ ከተሞች ከኒውዮርክ እና ጀኔቭ በመቀጠል ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ለዚህ የበቃችው ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን ታሪኳ ነፃነቷን አስጠብቃ በመዝለቋ፣ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ ባደረገችው ትግል፣ ከየዓለም መንግስታት ማህበር (ሊግ ኦፍ ኔሽን) እስከ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት (የቀድሞ አፍሪካ አንድነት ድርጅት) ድርጅቶችን በመመስረትና በአባልነት፣ በተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ያላት ሚና እና ጉልህ ተሳትፎ እንደሆነ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ዲፕሎማሲን ያስተማሩት እና በሶማሊላንድ  ሃርጌሳ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች መምህር በመሆን እየሰሩ የሚገኙት የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር አቶ በፈቃዱ ዳባ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ከፍ ያለ ቦታ ያላት ቢሆንም፤ ከዓመታት በፊት እንግዶቿን በአግባቡ ማስተናገድ የሚያስችል በቂ የመሰረተ ልማት አቅርቦትና አገልግሎት ነበራት ማለት አይቻልም፡፡ ገፅታዋ እና የምታቀርበው አገልግሎት ስሟንና ሚናዋን የሚመጥን እንዳልነበር ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ስድስት አስርት ዓመታት ወደኋላ መለስ ብንል በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1950ዎቹ መጨረሻ አካባቢ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፅህፈት ቤት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሆን ሲወሰን በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን ለማስተናገድ የሚመጥን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ማግኘት ፈተና ሆኖ ነበር። በወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ለድርጅቱ ጽህፈት ቤትና ለስብሰባ አገልግሎት የሚውል ህንጻ በአጭር ጊዜ እንዲገነባ አዝዘው እ.ኤ.አ በ1961 ዛሬ የአፍሪካ አዳራሽ እየተባለ የሚጠራው ህንፃ እንደተመረቀ “የአፍሪካ አዳራሽ አዲስ አበባ” በሚል ርዕስ በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ገፀ ድር የወጣው ሰነድ ያሳያል፡፡

ከዚህ በኋላ በተለያዩ ጊዜያት ከአፍሪካ አዳራሽ በተጨማሪ የአፍሪካ ህብረት ዋና ፅህፈት ቤት ህንፃን ጨምሮ ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ ሆቴሎች፣ መሰረተ ልማቶች ተገንብተው ወደ አገልግሎት ገብተዋል፡፡ እንደዚያም ሆኖ የተሰሩት ስራዎች መዲናዋ ያላትን ስምና ሚናዋን የሚመጥኑ ነበሩ ማለት እንደማይቻል የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ በተለያየ ኃላፊነት ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲው መስክ ያገለገሉት አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ከዚህ ቀደም ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት መረጃ ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡

አምባሳደር ጥሩነህ እንደሚናገሩት፣ የአፍሪካ መሪዎች ከዚህ ቀደም የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ በሚመጡበት ጊዜ ከአፍሪካ አዳራሽ ውጪ የሚሰበሰቡበት ስፍራ አልነበረም፡፡ የጉባኤ ታዳሚዎች ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አንስቶ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ግቢ ውስጥ የሚገኘው የአፍሪካ አዳራሽ እስኪደርሱ ድረስ፣ ከመንገድ በግራና በቀኝ ያሉት ስፍራዎች ቆሻሻ፣ ለእይታ ምቹና ደስ የማይሉ ስለነበር በቆርቆሮ ይታጠሩ ነበር።

የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር አቶ በፈቃዱም ይህንን ሀሳብ ይጋሩታል፡፡ “ከዚህ በፊት አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች በአፍሪካ ህብረት ስልጣን ለማግኘት ሳይሳካላቸው ሲቀር እንዲሁም በተለይ የነበራትን የመሰረተ ልማት ሁኔታ በማንሳት የአዲስ አበባ የአፍሪካ መዲናነት ላይ ጥያቄ ያነሱ ነበር። በቅርብ ዓመታት ከተማዋን ለመቀየር በተሰሩ ስራዎች ሲነዙ የነበሩ አሉታዊ ፕሮፖጋንዳዎችን ማፍረስ ተችሏል። በአሁኑ ሰዓት በማይታመን መልኩ ፅዱ፣ ውብና አረንጓዴ ከተማ ሆናለች” ብለዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አዴሲና ሰሞኑን፣ “አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ብትሆንም ከብዙ ዓመታት በፊት የነበራት ደረጃ ይህንን ተቋም ለማስተናገድ የሚመጥን አይደለም በሚል ቅሬታ ይነሳ ነበር። ዛሬ በየትኛውም የከተማዋ አካባቢ ብንመለከት ‘አፍሪካ የምትኮራባት’ ከተማ ሆናለች” ነው ያሉት፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሁንዴ ከበደ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እንደተናገሩት፣“በአዲስ አበባ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ግዙፍ የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ ነው፡፡ ከአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተጨማሪ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አዲስ አበባን ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ምቹ ያደረጉ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከልና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ተገንብተዋል።”ብለዋል፡፡   

የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ አቶ በፈቃዱ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ ለዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ተመራጭ የሚሆኑት ምቹ መሰረተ ልማትና አስተማማኝ ሰላም ያለባቸው ሀገራት ከተሞች ናቸው። አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ዋና ፅህፈት ቤት መቀመጫ፣ በዓለም ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል ከመሆኗ ባሻገር በኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻ እና ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በመገንባት፣ በፅዳትና ውበት ገፅታዋ በመቀየሩ ለጉባኤዎች ተመራጭ አድርጓታል። አስተማማኝ ሰላም እና ምቹ የአየር ሁኔታ መኖር እንዲሁም የህዝቡ እንግዳ ተቀባይነት አኩሪ ባህል መኖርም ሌሎች ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው፡፡

መዲናዋ በኮንፈረንስ ማዕከልነቷ ተመራጭ እንድትሆን አቅም ከሆኗትና በ2017 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ፕሮጀክቶች መካከል የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ተጠቃሽ ነው፡፡ ማዕከሉ በተመረቀበት ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት፣ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የተሰሩ በርካታ ስራዎች “አዲስ አበባን እንደ ስሟ አበባ፣ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከልነቷ የተጠናከረ፣ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ያለባትን ድርብርብ ኃላፊነት በብቃት የምትወጣና ተወዳዳሪ ከተማ” እያደረጋት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የማያቋርጥ ሀብት መፍጠሪያ፣ ለገፅታ ግንባታና ለቱሪስት ስበት ትልቅ ሚና የሚጫወት ነው፡፡ ዓለም አቀፋዊ ኮንፈረንሶችን፣ የንግድ ውይይትና ስምምነቶችን፣ ባህላዊ መድረኮችን፣ ልዩ ኤግዚቢሽን የሚስተናገዱበት ቦታ ነው፡፡ “አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤዎችን ብቻ አይደለም፣ ማንኛውም ዓለም አቀፍ ጉባኤ፣ ኮንፈረንስ፣ ኤግዚቢሽን ለማስተናገድ የሚያስችላትን ግብአት እያሟላች ስለመሆኗ አንዱ ማሳያ ነው።” ብለዋል፡፡

አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮንፈረንስ ማዕከል እንድትሆን በቅርብ ዓመታት ከተማዋ እያሳየችው ካለው እድገትና የማስተናገድ አቅሟ እያደገ መምጣት ባሻገር ኢትዮጵያ በጉባኤዎቹ በሚመከርባቸው የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያከናወነችው አርዓያነት ያለው ተግባር አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2017 በጀት ዓመት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ኢጣሊያ ጋር በመተባበር ሁለተኛውን የምግብ ስርዓት ጉባኤ እንድታዘጋጅ የተመረጠችው በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረግ ጥረት ተምሳሌት የሆነች ሀገር በመሆኗ ነው፡፡ በጷጉሜ ወር ላይ ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን እንድታዘጋጅ የተመረጠችበት ዋነኛው ምክንያትም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ፈር ቀዳጅ ስራ እያከናወነች እንደሆነ በመታመኑ ነው፡፡

ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ገፀ-ድሩ ላይ የወጣው መረጃም የጠቅላይ ሚኒስትሩን  ሀሳብ የሚያጠናክር ነው፡፡ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲና፣ የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ፣ የነፃነት ምልክት የሆነችው ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ለሚያስፈልገው የጋራ ርዕይና አንድነት ወካይ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ በተለያዩ ዘርፎች ከአረንጓዴ መር እድገት ጋር የተስማማ የአየር ንብረት ፖሊሲ በማውጣትና በቁርጠኝነት በመተግበር በተለይም በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በታዳሽ ሀይል እንዲሁም ዘላቂነት ያለው ትራንስፖርት በመዘርጋት ቀዳሚ ናት። አዲስ አበባ ያላት ምቹ የአየር ፀባይና ለአረንጓዴ ልማት ያላት ቁርጠኝነት ጉባኤውን ለማዘጋጀት ተመራጭ ስፍራ እንዳደረጋትም አትቷል፡፡

አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮንፈረንስ ማዕከልነት ወይም ጉባኤዎችን በማስተናገድ ተመራጭ መሆኗ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አቶ በፍቃዱ ያስረዳሉ። አንደኛ በየጉባኤዎች ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶች ሀገራቸውን ወይም የሚሰሩበትን ተቋም የሚወክሉ በመሆናቸው ሲመለሱ በከተማዋ ስላዩት ነገር ለሌሎች ያጋራሉ፡፡ እንግዶች ሆቴል፣ ትራንስፖርትና ሌሎች አገልግሎቶችን ሲጠቀሙ ከሚያወጡት ወጪ ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ታገኝበታለች፡፡ የውጭ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች በተለያዩ መስኮች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ የሚሰማሩበት ዕድል ይፈጠራል፡፡  የሀገር መሪዎችና የትላልቅ ተቋማት ኃላፊዎች መምጣት የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ትኩረት ይስባል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ራሷን ለመቀየር እያደረገች ያለውን ጥረት በተጨባጭ በዓይናቸው አይተው እንዲረዱ ያደርጋል፡፡

በተጨማሪም ሀገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ገፅታና ክብር ከፍ ያደርጋል። ኢትዮጵያ በታሪክ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የተለያዩ የዓለም አቀፍ ተቋማትን በመመስረትና ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ስትጫወት የነበረውን ሚና፣ ስሟን የምታድስበት ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ አሁን ደግሞ በምግብ ራስን በመቻል፣ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኝ በመትከል፣ ከአረንጓዴ ልማት ጋር የተወዳጁ ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባት ላይ ትገኛለች፡፡ ይህም ኢትዮጵያ  በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት የሚያሳድግ፣ መልካም ገፅታዋንም የሚገነባ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ 

አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብና አበባ፣ ለኑሮ ምቹ ከተማ ለማድረግ ሰፋፊ ስራዎች ተከናውነዋል፤ በመከናወን ላይም ይገኛሉ፡፡ እንደ እንጦጦና አንድነት ፓርኮች፣ ወዳጅነት አደባባይ፣ የብሔራዊ ቤተ መንግስት እድሳት፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማትና ሌሎች ትላልቅ ልማቶች የከተማዋን ደረጃና ገፅታ በማሳደግ፣ ለጎብኚዎች ምቹ፣   በዓለም ተመራጭ የኮንፈረንስ ማዕከል የሆነች ከተማ እንድትሆን አዎንታዊ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review