በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የወንዝ ዳርቻ ልማቶች የከተማዋን ገፅታ በመቀየርና የአካባቢ ጥበቃን በማረጋገጥ በኩል ትልቅ ትርጉም እንዳላቸው ተመላክቷል
“በቀበና ወንዝ ዳርቻ ለአስር ዓመታት ያህል ኖሬያለሁ፡፡ እናም ቀበናን በጣም አውቀዋለሁ። በክረምት ከእንጦጦ ጋራ ስር ጀምሮ አሰሱን ገሰሱን እየጠራረገ የተከራየኋትን ደሳሳ ጎጆ እየታከከ ይወርዳል፤ ይነጉዳል፡፡ እኔ ደግሞ ከዛሬ ነገ ከነቤተሰቦቼ ጠራርጎ ወሰደኝ እያልኩ ክረምቱን በስጋት አሳልፋለሁ፡፡”
“በጋው ሲመጣ ደግሞ በየጥጋጥጉ አሸዋ እያለበሰ ያስቀመጣቸው የእንስሳት በድኖች እና መሰል ቆሻሻዎች ዘግናኝ ጠረን አይጣል ነው፡፡ ቢሆንም በአካባቢው የወንዝ ዳር ልማት እንደሚከናወን ሲነገረኝ ወደ ሌላ አካባቢ ቤት ለመቀየር የወሰንኩባት ያቺ የመጨረሻዋ ምሽት ከወዳጄ ቀበና ጋር በመንፈስ የተጨዋወትንባት ልዩ ዕለት ናትና አትረሳኝም፡፡”
“ቀበና እውነት እንደ ሌሎች የዓለማችን ወንዞች አንተም አምሮብህ አይህ ይሆን? ብዙ የኖርኩብህ፣ ክፉና ደጉን ያሳለፍኩብህ አንተ ቀበና እንደገና ጥርት ብለህ እዝናናብህ ይሆን? እያልኩ አናግሬው ነበርና፡፡”
ይህንን ሀቅ ያጫወቱን በቀበና አካባቢ በተለምዶ ‘06’ ወይም ‘ኖራ ሜዳ’ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ተከራይተው ይኖሩ የነበሩት አቶ አዳም ባንተይርጋ ናቸው፡፡ በርግጥም የዝግጅት ክፍላችን ለስራ ምክንያት በየጊዜው ተዘዋውሮ ሲመለከታቸው እንደነበረው የመዲናዋ ወንዞች የትላንት መልካቸው አቶ አዳም ባንተይርጋ እንደገለፁት እጅግ አስፈሪ ነበር፡፡ ለአብነትም በክረምት ወቅት በጎርፍ አደጋና ተያያዥ ችግሮች የሚደርሱ አደጋዎች ከመገናኛ ብዙሃን የዜና ዝርዝሮች መካከል እንደማይጠፋ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡
ለአብነትም መጋቢት 12 ቀን 2015 ዓመተ ምህረት ለሊት ‘በከተማዋ በጣለው ዝናብ እናት እና ልጆችን ጨምሮ አራት ሰዎች በጎርፍ መወሰዳቸው ተሰምቷል’ የሚለው ዘገባ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ያሰሙት አሳዛኝ ዜና ነበር፡፡ በዕለቱም ከምሽቱ 12:05 ሰዓት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ማንጎ ሰፈር ወንዝ ዳርቻ ላይ በሚገኙ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ጎርፍ ገብቶ እንደነበር ተገልጿል፡፡ በአደጋውም የ46 ዓመት ወላጅ እናትን ጨምሮ የ3፣ የ13 እና የ15 ዓመት ልጆች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን የከተማዋ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
የሌሎች ሀገራት ወንዞች ታሪክ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ በክረምት ወቅት የሚደርሰውን አደጋ በቅርበት የሚያውቁት አቶ አዳም ባንተይርጋም፣ “ቀበና እውነት እንደ ሌሎች የዓለማችን ወንዞች አንተም አምሮብህ አይህ ይሆን?” እንዳሉት በርግጥም በሌሎች ሀገራት ወንዞች ውበት የሚፈልቅባቸው፣ የሚጎርፍባቸው እና እንዳሻው የሚገማሸርባቸው ድንቅ የተፈጥሮ ሀብቶች ናቸው፡፡
“….የሀገር ፀጋ የሀገር ልብስ” እንዳለች ተወዳጇ ድምፃዊ እጅጋየሁ ሽባባው አባይ ወንዝ ትናንት ለካርቱምና ካይሮ ከተሞች የውበታቸው ሰገነት፣ ምግብና መጠጣቸው ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ ለኢትዮጵያ ልብሷም ጉርሷም ነው፡፡ ወደ አውሮፓ ከፍ ብንልም የቴምዝ ወንዝ የለንደን ታሪክ እና ባህል ዓርማ ነው። 346 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ይህ ወንዝ ከተማዋን እያረሰረሰ፣ ፈገግታን በፊቷ ላይ እየነሰነሰ እና የፍቅር አክርማን እየቀነጠሰ መሃል ለመሃል ደስታዋን እየጨመረ አቋርጧት ያልፋል፡፡
በወንዙ ዳር ያሉ ፓርኮች፣ የእግረኛ መንገዶችና መሰል የሰውን ልጅ በሀሴት የሚያረሰርሱ መናፈሻዎች ለለንደን ከተማ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ለጉብኝት፣ ለስብሰባና ለልዩ ልዩ ጉዳዮች ወደ ከተማዋ ለሚመጡ እንግዶች ተመራጭ መዳረሻዎች፣ ጭንቀትና ናፍቆትን ማስረሻዎች እና ተበልቶ የማያልቅ የልቦና ማዕድ ናቸው፡፡
በአምስተርዳም የአምስቴል ወንዝ ለከተማው የውበት ምንጭ ነው፡፡ በወንዞቹ ዳርና ዳር ያሉ ታሪካዊ ሕንፃዎች እና ድንቅ ስፍራዎች በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጎብኚዎችን የሚስብ ልዩ ውበትን ፈጥረዋል። የአምስቴል ወንዝ ለከተማዋ የውበት ምንጭ ብቻ አይደለም፤ ከጫፍ እስከ ጫፍ መመላለሻና ካሰቡት መድረሻ መንገድም ነው፡፡
የሞስክቫ ወንዝ በሞስኮ እምብርት ውስጥ የተንሰራፋ እና የከተማዋን የህንፃ ጥበብ በውሃ መስታወትነት የሚያሳይ ድንቅ ፀጋዋ ነው፡፡ የወንዙ ዳርቻዎች በመናፈሻ ቦታዎች፣ በእግረኛ መንገዶች እና በባህላዊ ተቋማት የተሞሉ በመሆናቸው ከተማዋን የእንቅስቃሴ ማዕከል አድርጓታል፡፡ ይህ ወንዝ በደማቋ ከተማ ውስጥ በተፈጥሮ እና በከተማ ህይወት መካከል ያለውን ጣፋጭ መስተጋብር የሚያሳይ ዋቢ ምስክርም ሆኖ ያገለግላል፡፡
የአዲስ አበባ ወንዞች ግን ለዚህ ክብር አልታደሉም ነበር፡፡ ሁሉም ጀርባውን ሰጥቶ ቆሻሻ የሚጥልባቸው፣ አፍንጫውን ይዞ እየሮጠ የሚያልፍባቸው፣ የአካባቢው ነዋሪም ቢሆን በዘፈን እና በአባባል ከማወደስ ባለፈ የመፀዳጃ ቤት ቆሻሻውን የሚያራግፍባቸው አመድ አፋሾች ነበሩ፡፡
እውቋ ብራዚላዊት የስነ ሕንፃ እና ከተማ ፕላን ተመራማሪ ቲፋኒ ኒኮሊ ዋና መቀመጫውን በአሜሪካን ሀገር ቺካጎ ባደረገው እና በርካቶች የምርምር ስራዎቻቸውን በሚያሳትሙበት ‘Urban Design Lab’s’ (የከተማ ዲዛይን ቤተ ሙከራ) ላይ የከተማ ወንዞች ፋይዳ ወይም ‘The value of urban rivers: European experiences and a South American perspective’ በሚል ርዕስ ባሳተሙት ጥናታዊ ፅሑፋቸው እንደገለፁት በብዙ የአውሮፓ ዋና ከተሞች ያሉ ወንዞች የውበት፣ የሀብት፣ የሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን የዓሳም፤ የሀሳብም መመላለሻ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ በፓሪስ፣ በለንደን፣ በስቶክሆልም፣ በኦስሎ እና መሰል ከተሞች ያሉ ወንዞችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
የወንዝ ሀብታም የሆነችው አዲስ አበባ ግን ይህንን ውበትና ጥቅም ለማጣጣም አልታደለችም ነበር፡፡ በመጋቢት ወር 2017 ዓ.ም በከተማዋ ያሉ 76 ወንዞችና ገባሮች የተበከሉ መሆናቸው የአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአዲስ አበባ 7 ትልልቅና ከ75 በላይ ትንንሽ ወንዞች ቢኖሩም ለከተማዋ ውበትና ሀብት መሆን ግን አልቻሉም ነበር፡፡ ከታላላቅ ወንዞቿ መካከልም ቀበና፣ ባንተይቀጡ፣ ቀጨኔ፣ ቁርጡሚ፣ ቡልቡላ፣ አቃቂ እና የቄራ ወንዞችን መጥቀስ በቂ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ወንዞች የማይነኩት ወረዳና ክፍለ ከተማ የለም፤ በዚያው ልክ ችግሩም የማይነካው የለም።
የአካባቢ ሳይንስ ባለሙያው አቶ ገነነ ካሳሁን እንደሚሉት የከተማዋ ወንዞች የቀደመ ታሪካቸውም ሆነ አሁንም አልፎ አልፎ በአንዳንዶቹ ላይ እንደሚታየው በጣም አካባቢን የሚበክሉና ለሰው ልጆች የጤና ጠንቅ የሆኑ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ከተማ በተጀመረው የአረንጓዴ ልማት ስራ በወንዞቹና በዙሪያቸው አስደማሚ ለውጦች እየተመዘገቡ ነው። ለዚህ ደግሞ የቀበና ወንዝ ልማትን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራውን ተከትሎም በወንዞቹ አካባቢ በርካታ ችግኞች በስፋት እየተተከሉ በመሆናቸው በሌሎች የዓለማችን ከተሞች የምናየውን ወንዞች ውበትና ጥቅም በአዲስ አበባ ከተማም እውን የሚሆንበት ጊዜ ቅርብ መሆኑን ከእንጦጦ ጀምሮ በመዲናዋ ወንዞች ላይ እየተሰሩ ያሉ ልማቶች ማሳያ ስለመሆናቸውም ጠቅሰዋል፡፡
በመዲናዋ የተጀመረው የወንዝ ዳር ልማት የአዲስ አበባ ወንዞችን ወደ ሞት ሳይሆን ወደ ውበት ወደ ብክለት ሳይሆን ወደ ሀብት እንዲፈስሱ የሚያደርግ ዕድል እንደሆነም የአካባቢ ሳይንስ ባለሙያው አቶ ገነነ ካሳሁን ይናገራሉ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አሰግደው ወልደጊዮርጊስ እንደሚሉት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎም ለዘመናት ተረስተው የቆዩት ወንዞችን ለማልማት፣ የተጎሳቆለውን ገፅታቸውን ለመቀየር፣ ከብክለት ለመታደግ የከተማ አስተዳደሩ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል። በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ከተያዙና ግንባታቸው በፍጥነት እየተከናወኑ ከሚገኙ የወንዝ ዳርቻ ልማቶች መካከል 20 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍነው የቀበና ወንዝ ዳርቻ ይጠቀሳል፡፡
አቶ አሰግደው እንደሚገልፁት፤ በቀበና ወንዝም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች እየተከናወኑ የሚገኙ የወንዝ ዳርቻ ልማቶች የከተማዋን ገፅታ በመቀየርና የአካባቢ ጥበቃን በመጠበቅ በኩል ትልቅ ትርጉም ያላቸው ናቸው፡፡
በርካታ ዜጎችም በወንዝ ዳርቻ፣ የቤታቸውን ግድግዳ ወንዙ ስር በማድረግ ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ይኖሩ ነበር፡፡ በዚህም በተለያዩ ጊዜያት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ አደጋዎች ሲያጋጥም ቆይቷል፡፡ በወንዝ ዳርቻ ልማት ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ ነዋሪዎችን በማንሳትና ንፁህና ደህንነቱ በተጠበቀ አካባቢ እንዲኖሩ በማድረግ፣ የጎርፍ መከላከያ የድጋፍ ግንቦችን በመገንባት፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በመስራት የጎርፍ አደጋ ስጋትን መከላከል የሚያስችል አቅም መፍጠር እንደተቻለም ተናግረዋል፡፡
ትናንት የቀበናን ጎስቋላ መልኩን፣ በክረምት ሙላቱን፣ በበጋ ደግሞ መጥፎ ጠረኑን እያዩ ለአስር ዓመታት በአካባቢው የኖሩት አቶ አዳም ባንተይርጋ፣ “ቀበና እውነት እንደ ሌሎች የዓለማችን ወንዞች አንተም አምሮብህ አይህ ይሆን?” በማለት በመጨረሻዋ ምሽታቸው ከቀበና ጋር መጨዋወታቸውን ነግረውናል፡፡ ዛሬ ደግሞ የቀበና ወንዝ ልክ ፀጉሯን በመልኩ፤ በረድፉ፤ እንደተጎነጎነች ሐር የመሰለው የፀጉሯ ውበትም ከአጠላለፉ ጋር እንደሚታይላት ሙሽራ አሊያም እንደ ሐምሌ ፀሐይ ጉምና ጭጋጉን እየገላለጠ በመውጣት ለመዲናዋ የውበት ብርሃኑን መፈንጠቅ በመጀመሩ መደሰታቸውን ካጫወቱን በላይ የፊታቸው ገፅታ ብዙ ይናገራል፡፡
በመለሰ ተሰጋ