የኪነ-ጥበብ መሰናዶዎች ጥቁምታ

You are currently viewing የኪነ-ጥበብ መሰናዶዎች ጥቁምታ

ባለፉት ቀናት በአዲስ አበባ የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም መሰል ዝግጅቶች ይካሄዳሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የመጽሐፍ ውይይት እና የሥዕል አውደ ርዕይ ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የተወሰኑትን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡ 

መጽሐፍት

አንጋፋው ምሁር  ሃይሉ አርዓያ (ዶ/ር) በአንድ ጊዜ ሶስት መጽሐፎችን ለንባብ አብቅተዋል። ባሳለፍነው ሳምንት ለንባብ የበቁት እነዚህ ስራዎች፣ በሥነ ልቦና ጉዳዮች ላይ ያተኮረው “የማፍቀር ጥበብ”፣ በትውልድ ግንባታ ሂደት ውስጥ የመምህራን የላቀ አስተዋጽዎን የሚያስቃኘው “ሐዋርያው” እና  በኢትዮጵያ የስነ ቃል ጥበብ ላይ የሚያተኩረው “Ethiopian Folk Poetry Recreated” ናቸው፡፡ 

ሃይሉ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለዓመታት የስነ-ልሳን መምህርና ተመራማሪ ሆነው ሀገራቸውን አገልግለዋል። በዩኒቨርሲቲው ቋንቋዎች ጥናት ኢንስቲትዩት መስራች ሲሆኑ፣ በደርግ ጊዜ ደግሞ “የብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት” ሰብሳቢም ነበሩ፡፡

በሌላ ዜና “ፉካ” የተሰኘ የአጫጭር ልብ ወለዶች ስብስብ መጽሐፍ ለንባብ ሊበቃ ነው፡፡ መጽሐፉ የፊታችን ረዕቡ ለንባብ እንደሚበቃ ደራሲዋ ዘቢብ መልኬ በማህበራዊ የትስስር ገጿ አሳውቃለች፡፡

በሌላ መረጃ፣ በዛሬው እለት በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል “የልጆች መጽሐፍት በኢትዮጵያ” በተሰኘ ርዕስ የልምድ ልውውጥና ሙያዊ ውይይት ይካሄዳል፡፡ ሙያዊ ውይይቱ በአካዳሚው ቅጥር ግቢ ውስጥ በ 8:00 ሰዓት ይጀመራል፡፡ የዕለቱ ተጋባዥ ደግሞ በርካታ የልጆች መጽሐፍትን ለሕትመት ያበቃው ደራሲ፣ ተርጓሚና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቀድሞ መምህር ዓለም እሸቱ ነው፡፡  በዕለቱ የሥነ ጥበባት ማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ይታገሱ ጌትነት በኢትዮጵያ የልጆች መጽሐፍት ታሪክና ተግዳሮት ዙሪያ የመነሻ ጽሑፍ እንደሚያቀርቡ ታውቋል።

ይህ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እና በኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጽሐፍት አገልግሎት ትብብር በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር አማካኝነት የሚሰናዳው የክረምት ወራት የሥነ ጽሑፍ ሥልጠና አንዱ አካል ነውም ተብሏል፡፡

በሌላ መረጃ ደግሞ ነገ ነጻ ፈቃድ እና ተወሳኝነትን በሚመለከት ፍልስፍናዊ ውይይት ይደረጋል፡፡ የውይይቱ መነሻ ሃሳብ የሚያቀርበው መልአኩ አዳል (ዶ/ር) ሲሆን፣ በውይይቱ ላይ መጥታችሁ መሳተፍ ትችላላችሁ ተብሏል፡፡ ውይይቱ ከ8:00 ሰዓት ጀምሮ ብሔራዊ በሚገኘው በወመዘክር አዳራሽ ይቀርባል፡፡ ውይይቱን ያሰናዳው ደግሞ ዐውደ ፋጎስ የውይይት ክበብ ነው፡፡

ሥዕል

የቡድን የግራፊክስ ጥበብ አውደ ርዕይ በመታየት ላይ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ረዕቡ ሐምሌ 30 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ በተከፈተው የጥበብ አውደ ርዕይ

የተለያዩ ሰዓሊያን ስራዎች በመታየት ላይ ይገኛሉ፡፡

በዚህ የጥበብ አውደ ርዕይ ሥራዎቻቸው ካቀረቡ ከያኒያን መካከል ታደሰ ባይሳ፣ ሚኪያስ ሰለሞን፣ ቤርሳቤህ አለማየሁ፣ ምህረት እሸቱ፣ ዳግማዊ ጸጋዬ፣ ሱራፌል መክብብ ይገኙበታል፡፡ ዓውደ ርዕዩ እየታየ ያለው በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል ውስጥ በሚገኘው የፈንደቃ የባህል ማዕከል ውስጥ ሲሆን እስከ ፊታችን ነሐሴ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ይቆያል፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review