የነሐሴ ወር ሲጋመስ የቡሄ በዓል ትዝታ ይመጣል። ክረምቱ ጠንክሮ ዝናቡ መሬቱን በውኃ ሲያጥበው፣ ሰማዩም በጉም ሲሸፈን ከዚያ እንደገና ወደ ብራ ወቅት ሲቃረብ ቡሄ የልጅነት ትዝታን ይዞ ከተፍ ይላል፡፡
ቡሄ ብራ ነው፡፡ ሰማይ ከጭጋግ ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት የመሸጋገሪያ ወቅት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ “ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፣ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት” የተባለውም ለዚሁ ነው፡፡ በሌላ በኩል ሙልሙል ዳቦ የሚጋገርበት ወቅት ነው፡፡ የልጆች ዜማ ደግሞ ሌላኛው ቡሄ የመድረሱ ምልክት እና አዲስ ዓመት ስለመቅረቡ አስታዋሽ ትዝታ ነው፡፡
የቡሄ በዓል፣ ከትምህርት ቤት የእረፍት ጊዜ ጋር ተገጣጥሞ የሚመጣ፣ የበርካቶች የልጅነት አሻራ የታተመበት በዓል ነው፡፡ ይህ በዓል የራሱ የሆነ የፍቅር፣ የደስታ እና የትዝታ ስሜት አለው። ልጆች በየሰፈሩ እየተሰባሰቡ ዱላ እና ድምፅ የሚያወጡ ቁርጥራጭ ብረቶችን በመያዝ “ሆያ ሆዬ” እያሉ በየቤቱ ይዞራሉ። በሚያቀርቡት ጭፈራም በቅድሚያ የቤቱን አባዎራና እማዎራ እንዲሁም የቤተሰቡን አባል ክራሞት፡-
እዚህ ቤት ያላችሁ እንደምን ናችሁ፣
በዓመት አንድ ቀን መጣንላችሁ… በማለት ይጠይቃሉ፡፡
ለቡሄ ሕፃናትና ወጣቶች፣ በቡድን በቡድን በመሆን “ቡሄ በሉ” እያሉ ከቤት ወደ ቤት እየተዘዋወሩ ይጨፍራሉ፡፡ በዘፈናቸውና በጭብጨባቸው ውስጥ የደስታ እና ተስፋ ስሜት አለ። ከልጆች ጭፈራ በተጨማሪ ሙልሙል ዳቦ ደግሞ የቡሄ በዓል ሌላኛው ድምቀት ነው። ልጆችም እንዲህ እያሉ ይጨፍራሉ፡-
ሆያ ሆዬ ሆ
መጣና በዓመቱ
ኧረ እንደምን ሰነበቱ
ሆያ ሆዬ
ሆያ ሆዬ ጌታ ጠንበለል
ዝናቡ መጣ ወዴት ልጠለል
አባብዬ ቤት እጠለላለው
ሙልሙል ዳቦዬን ይዤ እሄዳለው…፡፡
የቡሄ ጭፈራ የመዝናኛ እና የደስታ መግለጫ ከመሆን ባለፈ፣ ጥልቅ የሆነ ማህበራዊ አንድምታ አለው። ጭፈራው ሰዎች እርስ በእርስ እንዲገናኙ፣ እንዲተዋወቁ እና ያላቸውን ልዩነት ወደ ጎን በመተው አብረው እንዲደሰቱ ያደርጋል። ልጆች ከማህበረሰባቸው ጋር ያላቸው ትስስር ከፍ እንዲል ይረዳል፡፡ ይህ ደግሞ በህብረተሰቡ ውስጥ ሰላምን፣ ፍቅርን እና መተሳሰብን ያሳድጋል። ጭፈራው የትውልድን እሴት ከአዲሱ ትውልድ ጋር በማገናኘት፣ ባህላዊ እሴቶች እንዲጠበቁ ያግዛል።
ከሀበሻ ኳየር የኪነ ጥበብ ባንድ መስራቾች ውስጥ አንዱ የሆነው ቢተው ዳዊት ለቡሄ ልጆች ጅራፍ ያጮሃሉ፤ ይጨፍራሉ፡፡ ሙልሙል ዳቦ ይቀበላሉ፡፡ በታላላቆች ይመረቃሉ፡፡ ሲጨፍሩ ደግሞ በህብረትና አንድነት ነው፡፡ በአጠቃላይ ቡሄ ባህልን አጉልቶ የሚያሳይ መነጽር ነው ማለት ይቻላል ይላል፡፡
የቡሄ ዳቦ የሚሉት ሙልሙል
ጎበዝ ተሰብሰብ ቡሄ እንበል።
ሆያ ሆዬ ጉዴ… እየተባለ የሚጨፈረው በዓሉ በአንድነት፣ በአብሮነትና በመተሳሰብ የሚከበር መሆኑን ለማመላከት ነው፡፡ የጅራፍ ድምጽ፣ ህብረ ዝማሬ፣ ምርቃትና ሙልሙል ስጦታ ቡሄን የሚያስናፍቁ ክዋኔዎች ናቸው፡፡
የሆያ ሆዬ ግጥሞች ከአካባቢ አካባቢ ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ዋናው መልዕክቱ በረከት፣ ፍቅርና አንድነት ላይ ያተኩራል። የቤቱን አባዎራና እማዎራ ማወደስና ማመስገንም የጭፈራው አካል ነው፡፡
ሰዋሰው ገጸ-ድር በ2015 ዓ.ም የቡሄ በዓል ትውፊትና አከባበርን አስመልክቶ በጻፈው ጽሑፍ ላይ እንደገለጸው፣ ልጆቹ ሆያ ሆዬ በሚጨፍሩበት ወቅት ወደ ቤት የሚገቡት ሲፈቀድላቸው ብቻ ነው፡፡ ከዛም በሩ ተከፍቶ እንዲጨፍሩ ሲፈቀድላቸው የቤቱን ጌታና እመቤት በግጥምና በዜማቸው ማወደስና ማሞገሱን ይያያዙታል፡፡ የቤቱን አባወራ ከሚያወድሱባቸው ግጥሞች ውስጥ የሚከተሉትን ስንኞች መጥቀስ ይቻላል፡፡
የኔ ጌታ የሰጠኝ ሙክት
ግንባሩ ላይ አለው ምልክት
መስከረም ጠባ እሱን ሳነክት
በጌታዬ ቤት በጉልላቱ
ወርቅ ይፍሰስበት ባናት ባናቱ።
የኔማ ጌታ ጌታ ነው ጌታ
ሲቀመጥ ሲያምር ሲቆም ሲረታ።
የኔማ ጌታ የሰጠኝ ላም
አስር ዓመትዋ ኖረች በዓለም… እያሉ ያወድሳሉ፡፡ በእርግጥ የሚወደሰው አባወራው ብቻ አይደለም፡፡ እመቤቲቱም በግጥምና በዜማ ይወደሳሉ፡፡ በዘፈናቸውና በጭፈራቸውም ቤት ውስጥ ያሉትን የቤተሰብ አባላት በመልካምነታቸው ያደንቃሉ፤ ያሞግሳሉ።፡
የኔማ እመቤት መጣንልሽ
የቤት ባልትና ልናይልሽ።
የኔማ እመቤት የጋገረችው
የንብ እንጀራ አስመሰለችው።
የኔማ እመቤት ብትሰራ ዶሮ
ሽታው ይጣራል ገመገም ዞሮ…፡፡
ልጆቹ ዘፈናቸውን አጠናቅቀው ከቤት ደጃፍ ላይ ሲደርሱ፣ የቤቱ አባዎራዎችና እማዎራዎች የሚያቀርቡላቸው ሽልማቶች አሉ። ዋናው ሽልማት ሙልሙል ዳቦ ነው። አሁን አሁን ግን፣ ሙልሙል ዳቦ የመስጠቱ ባህል በተለይ በከተሞች አካባቢ ቀስ በቀስ በገንዘብ እየተተካ መምጣቱን መታዘብ ይቻላል። ብዙ ጊዜ ልጆች ዘፈናቸውን ሲያጠናቅቁ፣ የቤቱ አባወራዎች ገንዘብ ስጦታ በማበርከት ያበረታቷቸዋል።
የኪነ ጥበብ ባለሙያው ቢተው ዳዊትም ይሄን ነገር የታዘብኩት ጉዳይ ነው ይላል፡፡ ባለሙያው ገንዘብ ባህልን ሊያስጥል አይገባም፡፡ ባህልን መጠበቅ የሀገር ፍቅር አንዱ መገለጫ ነው፡፡ ባህል የሀገር ፍቅርን ያጎላል፡፡ ቱሪዝምን ያሳድጋል፡፡ ምክንያቱም ፈረንጆች የሚመጡት ልዩ የሆነውን ባህል ለማየት ነው፡፡ በመሆኑም እኛ የኪነ ጥበብ ሰዎችና ወላጆች ትክክለኛውን ባህል ለትውልዱ በማሳወቅ በኩል ብዙ ይጠበቅብናል፡፡
ይሁን እንጂ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይ በገጠር ባህሉ አሁንም እንደቀድሞው ሙልሙል ዳቦ በማዘጋጀት ይከበራል። በከተሞች አካባቢ ትክክለኛ ባህሉን እየለቀቀ ነው የሚለው አስተያየት እንዳለ ሆኖ የቡሄ በዓል ጭፈራ ከትውልድ ትውልድ በተለያየ መልኩ እየተላለፈ ዛሬ ደርሷል፡፡ ቡሄ በመጽሐፍ፣ በስነ ቃል፣ በፊልምና በሌሎችም የጥበብ መንገዶች ተሰርቷል፡፡ ነገር ግን በኪነ ጥበብ በሚገባው ደረጃ ተገልጿል ማለት እንደማይቻል አብራርቷል፡፡
ቡሄን ጨምሮ በዓላትን ከማስተዋወቅ አንጻር የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች መስራት ያለብንን አልሰራንም፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁላችንም ተወቃሽ ነን፡፡ የአንድ ሀገር መገለጫ በዓልም ይሁን ባህል የህዝብ ነው፡፡ ስለዚህ የኪነ ጥበብ ባለሙያ ይህን የሀገራችንን መገለጫ ማስተዋወቅ ግዴታው ነው በማለትም ያክላል፡፡
በእርግጥ ቡሄ በሙዘቃ ስራዎች ውስጥ በተወሰነ መልኩ ተንጸባርቋል ማለት ይቻላል፡፡ ቀደም ካሉት ታዋቂ ድምጻውያን ሰለሞን ደነቀን ከወጣቶቹ ደግሞ ቃልአብ ክንፈ ይጠቀሳል፡፡ ወጣቱ ድምጻዊ ሙዚቃውን የሰራው በ2014 ዓ.ም ነው፡፡ እስኪ ሆያ ሆዬ ከተሰኘ ሙዚቃው ስንኞች ውስጥ ጥቂቶችን እንጥቀስ፡-
መጣና በዓመቱ
እንደምን ሰነበቱ
ክፈት በለው ተነሳ
ይህን አንበሳ
ክፈት በለው በሩን
የጌታዬን
ሆያ ሆዬ ሆ
ሆያ ሆዬ ሆ
እዚህ ቤቶች እንደምን ናችሁ
በዓመት አንድ ቀን መጣንላችሁ
በዓመት አንድ ጊዜ ለመጣ እንግዳ
ምሳው ሙክት ነው እራቱ ፍሪዳ
ሆያ ሆዬ ጉዴ
ጨዋታ ነው ልማዴ… በማለት ነሐሴ ወር እና ቡሄ በዓመት አንድ ጊዜ የሚመጡ፣ ተናፋቂና ተወዳጅ መሆናቸውን አቀንቅኗል፡፡
በአጠቃላይ ሆያ ሆዬ የብዙ ሰዎች ትዝታ እና የህጻናት ፌሽታ ነው፡፡ ወቅቱ ለመጻፍ፣ ለመግጠም፣ ለመዝፈን እና ለሌሎች የኪነ ጥበብ ስራዎች መነሻ ሐሳብ በመሆን ያገለግላል፡፡
በጊዜው አማረ