የጂኦስፓሺያል መረጃ በአረንጓዴ ዐሻራ

You are currently viewing የጂኦስፓሺያል መረጃ በአረንጓዴ ዐሻራ

ለአረንጓዴ ዐሻራ የጂኦስፓሺያል መረጃን የማከናወን ሥራው በየዓመቱ ዕድገት እያሳየ ነው

 በጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር 1675 አካባቢ እንደተመሰረተች ይነገርላታል፤ የኮሎምቢያዋ ከተማ ሜደሊን፡፡ ከቦጎታ በመቀጠል በስፋቷ ሁለተኛዋ ትልቋ ከተማ ነች፡፡ በጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር ከ1980 እስከ 1990ዎቹ ድረስ ያሉት ዓመታት ለከተማዋ ዕድገት በወርቃማነታቸው የሚዘከሩ ናቸው፡፡ ለከተማነት ዕድገቷ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን በቁልፍ ግብዓትነት በመጠቀምም ትታወቃለች። በዚህ ተግባሯም በጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር በ2023 በወል ስትሪት ጆርናል እና በአርባን ላንድ ኢንስቲትዩት የዓመቱ ምርጥ የኢኖቬሽን ከተማ ተብላ ለመመረጥ ችላለች፡፡ ይህ ያልተቋረጠ ዕድገት እና መስፋፋት የኋላ ኋላ በከተማዋና በነዋሪዎቿ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ወደ መፍጠር ተሸጋግሯል፡፡ ከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአየር ሙቀት እና በአካባቢ ብክለት የሚደርስባት ፈተና እየበዛ መጣ፡፡

ከተማዋ የተጋረጠባትን ፈተና የተመለከቱት የኮሎምቢያ መንግስት እና የከተማዋ አስተዳደር በቸልታ ማየት አልፈለጉም፡፡ በጥናት ላይ የተመሰረተ መፍትሔ ወደማፈላለግ ገቡ፡፡ “የአረንጓዴ ኮሪደር” ልማት ፕሮጀክትን ይፋ አደረጉ። “How Medellin Solved Heat Problem with Tree-Planting” በሚል ርዕስ ተሰናድቶ፣ በጎርጎሮሳዊያን የዘመን ቀመር በወርሃ ነሐሴ 2025 በኮሎምቢያ ዋን ዶት ኮም ገፀ ድር ላይ ለንባብ የበቃው ጥናታዊ ፅሁፍ እንደሚያመላክተው፤ በሜደሊን ከተማ ተግባራዊ የተደረገው “የአረንጓዴ ኮሪደር” ልማት ፕሮጀክት ዓላማ የከተማዋን ማስተር ፕላን ባገናዘበ መልኩ የአረንጓዴ ዕጽዋት ሽፋንን ማሳደግ ነው፡፡ በጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር ከ2019 ጀምሮ የተተገበረው ፕሮጀክቱ፤ የከተማዋን ዋና ዋና የመንገድ ዳርቻዎችና አካፋዮች፣ አደባባዮች፣ ፓርኮች፣ የወንዝ ዳርቻዎች፣ ተራራና ኮረብታዎች እንዲሁም አዳዲስ ሥፍራዎችን ያካተቱ 30 ቦታዎችን አካልሏል፡፡ 70 ሄክታር መሬት እና 20 ኪሎ ሜትር የሚረዝም መንገድን በዕፅዋት ልማት ለመሸፈን ተሰርቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2021 ብቻ ከተማዋ በነበራት የደን ሀብት ላይ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ዕፅዋት እና ከ880 ሺህ በላይ ዛፎች ተተክለዋል፡፡

በተጨማሪም፤ በየዓመቱ ያለማቋረጥ እየተተገበረ ላለው ፕሮጀክት ከተማዋ ከ16 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ወጪ አድርጋለች፡፡ ሥራው ከተማዋ ለነዋሪዎቿ የተመቸች እንድትሆን እያደረጋት እንደሚገኝ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡

አዲስ አበባ ከተማም የሜደሊንን ዓይነት ስኬት ለማስመዝገብ በሚያስችላት ጉዞ ላይ እንደምትገኝ በቅርብ ዓመታት እየተሠሩ ያሉ ለአረንጓዴ ልማት መስኩ ትኩረት የሰጡ ተግባራት ማሳያዎች ናቸው፡፡ ሥራዎቹም ዘላቂ ውጤት እንዲያመጡ በጥናትና ምርምር ስለመደገፋቸው ከአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ስፔስ ሣይንስ እና ጂኦስፓሽያል ኢንስቲትዩት እየተወጣ ያለው ተቋማዊ ኃላፊነት መጥቀስ በቂ ነው፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ውጤታማ እንዲሆን የተለያዩ ተቋማት በመቀናጀት ተግባሩን የመምራት እና የማስተባበር ኃላፊነትን ይወጣሉ። ከእነዚህ ተቋማት መካከል አንዱ፤ ስፔስ ሣይንስ እና ጂኦስፓሽያል ኢንስቲትዩት ነው፡፡ ይህ ተቋም በዋናነት ጥራት ያላቸው መረጃዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ያግዛል።፡ ከችግኝ ማፍላት ጀምሮ፣ የተከላ፣ የፅድቀት እና የደን ሽፋን ደረጃውን በትክክል የሚያመላክቱ መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በማደራጀት እና በመተንተን ውጤቱን ለሚመለከታቸው አካላት ያሰራጫል፤ ገለፃ ያደርጋል፡፡

አቶ ቴዎድሮስ ካሳሁን፤ የኢትዮጵያ ስፔስ ሣይንስ እና ጂኦስፓሽያል ኢንስቲትዩት የካርታ ሥራ ክፍል መሪ ሥራ አስፈፃሚ ናቸው፡፡ ኢንስቲትዩቱ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርን መሰረት አድርጎ የሠራቸውን ተግባራት በተመለከተ ሲያብራሩ፤ በያዝነው የ2017 ዓ.ም. እየተከናወነ ካለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ጋር በተያያዘ ኢንስቲትዩቱ ወሳኝ ሥራዎችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተቋቋመው የስትሪንግ ኮሚቴ ጋር በመቀናጀት ሰርቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተለዩ 13 ሺህ 84 የተከላ ቦታዎች ካርታ ተዘጋጅቷል፡፡ ካርታ የተዘጋጀላቸው የመትከያ ቦታዎች አጠቃላይ ስፋት 294 ሺህ ሄክታር የሚሸፍን ሲሆን፤ መሬት ላይ በቦታው በአካል በመገኘት ተለክቶ በተወሰደ መረጃ ላይ ተመስርቶ የተከናወነ ነው፡፡ እያንዳንዱ የመትከያ ቦታ፤ የሚገኝበት ክልል፣ ወረዳ፣ ቀበሌ፣ የመትከያ ቦታው (ሳይት) እንዲሁም የቦታው መገኛ ማዕከላዊ ነጥብ (Center Point) በዝርዝር በካርታዎቹ ተመላክቷል፡፡

ለ2017 ዓ.ም. የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የችግኝ ተከላ እንዲከናወንባቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተለዩ እና ካርታ ከተዘጋጀላቸው 13 ሺህ 84 ቦታዎች መካከል፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙት ብዛት በቁጥር 277 (ሁለት መቶ ሰባ ሰባት) ሲሆን፤ ስፋታቸውም 348 ሄክታር ይሸፍናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፤ በኦሮሚያ ክልል የመሬት ሽፋናቸው 212 ሺህ 560 ሄክታር የሆኑ 6 ሺህ 595 የመትከያ ቦታዎች እንዲሁም በአማራ ክልል ሽፋናቸው 57 ሺህ 497 ሄክታር የሆኑ 4 ሺህ 50 የመትከያ ቦታዎች ካርታ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡

ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የሚሆን የጂኦስፓሺያል መረጃዎችን የማሰባሰብ እና የማጠናቀር ሥራ በቋሚነት መከናወን የጀመረው በ2015 ዓ.ም. እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ቴዎድሮስ፤ ሥራው በየዓመቱ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ባለፈው የ2016 ዓ.ም. 8 ሺህ የሚሆኑ የመትከያ ቦታዎች ካርታ ተዘጋጅቶላቸዋል። ለዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተዘጋጁ የተከላ ቦታዎች ካርታ ከአምና አንፃር ብልጫ አለው፡፡ ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያሉ አመራሮች እና ባለሙያዎች የአረንጓዴ ልማት ሥራቸውን በተጨባጭ መረጃ ላይ ተመስርቶ ለማከናወን ያላቸው ተነሳሽነት እና የመፈፀም ብቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ማሳየቱ ትልቅ እገዛ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡

አቶ ቴዎድሮስ አክለው እንዳስረዱት፤ የመትከያ ቦታዎችን ካርታ ማዘጋጀትን ጨምሮ፤ ከችግኝ ማፍላት ጀምሮ፣ የተከላ፣ የፅድቀት እና የደን ሽፋን ደረጃውን በትክክል የሚያመላክቱ መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በማደራጀት እና በመተንተን ውጤቱን ለሚመለከታቸው አካላት የማሰራጨት ኃላፊነትን በአግባቡ ለመወጣት እንዲቻል የስፔስ ሣይንስ እና ጂኦስፓሽያል ኢንስቲትዩት የተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችንና መተግበሪያዎችን (ሶፍትዌሮችን) ይጠቀማል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የሳተላይት ምስሎችን የሚሰጡ የሳተላይት እና የጂፒኤስ (GPS) ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም ኪውጂአይኤስ (QGIS) የመሳሰሉ የመረጃ መተንተኛ ሶፍትዌሮች ይጠቀሳሉ፡፡

“ሥራ ያለምክንያት አይፈጠርም። እንደ ሀገር መጠኑ ይለያይ እንጂ፤ የአረንጓዴ ልማት ሥራ የማከናወን ልምድ አለ፡፡ ይህ ልምድ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በስፋት መከናወን ከተጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ልማቱ ውጤታማ እንዲሆን ሥራዎች በመረጃ ላይ ተመስርተው መከናወን አለባቸው” ሲሉ የኢትዮጵያ ስፔስ ሣይንስ እና ጂኦስፓሽያል ኢንስቲትዩት የካርታ ሥራ ክፍል መሪ እና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮስ ካሳሁን ተናግረዋል፡፡

ዘመናዊ ቴክኖሎጂንና አሠራሮችን ተጠቅሞ እየተተገበረ ያለው መረጃዎችን የማጠናቀር ተግባር ለአረንጓዴ ልማት ያለውን አስተዋፅኦ ከቀደመው ተለምዷዊ አሠራር ጋር አነጻጽረው ሲያብራሩም፤ ከዚህ ቀደም የችግኝ ተከላ፣ ፅድቀት እና የመሳሰሉ ሥራዎች ውጤታማነታቸው የሚለካው ከታች ወደላይ በሚመጡ ሪፖርቶች እና መረጃዎች ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ያልተተከለው እንደተተከለ፣ ያልፀደቀው እንደፀደቀ ተደርጎ እንዲወሰድ እና የመረጃ መፋለስ እንዲፈጠር ያደርጋል። ከዚህ አንፃር የስፔስ ሣይንስ እና የጂኦስፓሺያል ኢንስቲትዩት ከአረንጓዴ ዐሻራ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በጥራት እና በፍጥነት እንዲሰበሰቡ፣ እንዲተነተኑና እንዲሰራጩ ከማድረግ አንፃር እየሠራ ያለው ሥራ ቀደም ሲል ይታይ የነበረውን ክፍተት የሸፈነ ነው፡፡ በሀገሪቷ ሁሉም አካባቢዎች፤ በተለይም ካርታ በተዘጋጀላቸው እያንዳንዱ የችግኝ መትከያ ቦታ ላይ ስለሚከናወኑ እና ስለተከናወኑ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ውጤታማነት (የተተከለ ችግኝ፣ የፅድቀት መጠን፣ ሽፋኑን..) የሚያሳዩ መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት ተችሏል፡፡ ከአረንጓዴ ልማት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ለውሳኔ ሰጪ እና ክትትልና ድጋፍ ለሚያደርጉ አካላት፣ ለጥናትና ምርምር ተቋማትና ባለሙያዎች… ጥራት ያለው መረጃ እንዲደራጅ አቅም ፈጥሯል፡፡ ውጤታማ ተሞክሮን ለማስፋት እንዲሁም ተጠያቂነትን ለማስፈን ተጨባጭ ማስረጃ ማደራጀት ተችሏል፡፡ የአረንጓዴ ልማት አንድ ውጤት ከሆነው የካርበን ሽያጭ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችለውን የተደራጀ መረጃ ዓለም አቀፍ ስታንዳርዱን በጠበቀ መልኩ ለማዘጋጀት እና ለማቅረብ ወሳኙ ተግባር እንዲከናወን አግዟል፡፡

ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ያለማቋረጥ እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ይገኛል፡፡ የሀገሪቱን የደን ሽፋንም ዕድገት አሳይቷል፡፡ ይህንን አስመልክቶ የተሠራ ጥናትን ዋቢ በማድረግ የግብርና ሚኒስቴር ባሰራጨው መረጃ፤ መርሃ ግብሩ ከመጀመሩ በፊት የነበረውን 17 ነጥብ 2 በመቶ የደን ሽፋን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማደጉን አመላክቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ፤ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በየዓመቱ የመትከሉ ተግባር ባህል ወደመሆን ያሸጋገረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ በዘንድሮው ዓመትም ይሄው ሀገር አቀፍ መርሃ ግብር በታላቅ መነሳሳት እና በከፍተኛ ሕዝባዊ ተሳትፎ መከናወኑን ቀጥሏል፡፡

በደረጀ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review