“በቀድሞው ቤቴ ያሳለፍኩትን ህይወት ሳስታውሰው የአሁኑን ዳግም እንደተወለድኩ ነው የምቆጥረው”
የቤት ዕድሳት ተጠቃሚ የሆኑት ወይዘሮ እናኑ መሸሻ
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ መሰረተ ልማትን ዘመናዊ፣ ምቹ እና ሁለን አቀፍ በሆነ መንገድ በጥራት በመገንባት መዲናዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ከሌሎች ሀገራት ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ 24/7 (ሰባቱንም ቀን ሃያ አራት ሰዓት) እየሰራ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በተለያዩ በጎ ፍቃድ ስራዎች ላይ እየተሳተፈ ይገኛል። ከነዚህም መካከል የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት እና ግንባታ በዋነኝነት ይጠቀሳል፡፡ ባለፉት ዓመታት በርካታ ቤቶችን በመገንባት ለአቅመ ደካሞች አስረክቧል፡፡ በተጠናቀቀው 2017 በጀት ዓመት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ገንብቶ ያስረከባቸውን ቤቶች ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
በቤት እድሳት ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወይዘሮ እናኑ መሸሻ አንዷ ናቸው፡፡ በክፍለ ከተማው ወረዳ 05 ቡልጋርያ ሰፈር ነዋሪ ናቸው፡፡ ቤታቸው ለረጅም ጊዜ ምንም እድሳት ሳይደረግለት በመቆየቱ የአፈር ቤታቸው ምርጉ ከግማሽ በታች ፈራርሷል። የቀረውም ቢሆን ምንም መከላከል የማይችል ነበር። ሆኖም ወይዘሮ እናኑ ከአንድ ልጃቸው ጋር በቤቱ ከመኖር ውጭ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡ በበጋ ወቅት ብርድ እና ንፋስ ያስቸግራቸዋል። የክረምቱ ደግሞ ከዚህም ይከፋል። ጭንቀቱ የእሳቸው ብቻ ሳይሆን አብረዋቸው የሚኖሩ ጎረቤቶቻቸውም ጭምር ነው። ዝናብ ጠብ ሲል “እንዴት ሆነው ይሆን” ብለው በስራ ላይ ሆነው እንኳን እንደሚያስቧቸው እና ደውለው እንደሚጠይቋቸው ጎረቤቶቻቸው ይናገራሉ፡፡ ዝናብ በበረታ ጊዜ ቤታቸው በጎርፍ ውሃ ይሞላል፡፡ ያኔ ደርሰዉ ውሃውን ከቤት እየቀዱ ወደ ውጭ በመድፋትም ያግዟቸዋል፡፡
ህይወታቸውን በፈለጉት መልክ ለማስተካከል ያቃታቸው እናት ፈጣሪ እጁን እንዲዘረጋላቸው ከማልቀስ እና ከመማፀን በቀር ማድረግ የሚችሉት ነገር አልነበረም፡፡ “ቤቴ ከመፀዳጃ ቤት ጋር ተያይዞ የተሰራ በመሆኑ ሽታው በተደጋጋሚ ለበሽታ አጋልጦኛል። ታምሜ ተኝቼ እንኳን ሰዎች ቤቴ መጥተው ለመቀመጥ አይፈልጉም፤ በቁማቸው ጠይቀውኝ ይመለሳሉ” ይላሉ ወይዘሮ እናኑ ያለፈውን ጊዜ በማስታወስ።፡
በቃ ሲል ይበቃል! ይባል አይደል፡፡ የወይዘሮ እናኑ ለቅሶ ሰሚ አገኘ፡፡ የአዲስ አባባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ማልቀስ ይብቃዎት! ብሎ የልባቸውን መሻት ሊፈጽም በራቸውን አንኳኳ፤ በግማሽ የፈረሰ ቤታቸውን ሙሉ በሙሉ አፍርሶ፤ ለወይዘሮ እናኑ ብቻ ሳይሆን አብረዋቸው ለሚዋሰኑት ሶስት ጎረቤታቸውም ጭምር በዘመናዊ መልክ ቤት ገንብቶ አጠናቀቀ፡፡
እነዚህን ገንብቶ ያጠናቀቃቸው ቤቶች ምርቃት እና የቁልፍ ርክክብ ስነ ስርዓት በሀምሌ1 ቀን 2017 ዓ.ም ተከናውኗል፡፡ በስነ ስርዓቱ ላይ የባለስልጣኑ የኮርፖሬት ሰርቪስ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀማል ዶሌቦ፣ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ምስክር ነጋሽ (ዶ/ር)፣ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደፍርስ ኮራ፣ የባለስልጣኑ እና የክፍለ ከተማው አመራሮች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀማል ዶሌቦ በምርቃቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ “ባለስልጣኑ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ሰው ተኮር ስራዎችን ይሰራል። ለአቅመ ደካሞች መአድ ማጋራትን፤ ለ50 ልጆች ቋሚ ድጋፍ ማድረግ፤ በአበይት በዓላት ላይ ዝቅተኛ ደሞዝ ላላቸው ሰራተኞች በዓልን ተደስተው እንዲያሳልፉ የተለያየ ድጋፍ መስጠት እና የአቅመ ደካሞችን ቤት እድሳት እና ግንባታ በእቅድ ያከናውናል። በቀጣይ ይህን ስራውን ሰፋ ባለመልኩ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በዚህ ስራ የተሳተፉ እና የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ ተቋራጮች እና አማካሪ ድርጅቶች ልትመሰገኑ ይገባል” ብለዋል፡፡
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ምስክር ነጋሽ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ “የቤት እድሳት እድሉን ያገኛችሁ የቤት ባለቤቶች እንኳን ደስ አላችሁ፡፡” በማለት ክፍለ ከተማው ሰው ተኮር የሆኑ እና የህብረተሰቡን አኗኗር የሚያሻሽሉ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
የቤት ርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ ደስታቸውን መግለፅ የተሳናቸው ወይዘሮ እናኑ አይኖቻቸው ሲያነቡ ታይተዋል፡፡ የዛሬው እንባ ከዚህ ቀደሙ ይለያል፡፡ ዛሬ ከአይናቸው የሚፈልቀው የደስታ እንባ ነው፡፡ ትናንት የነበሩበትን አስታውሰው የዛሬውን ቤታቸውን ሲመለከቱት ልዩነቱ አራምባ እና ቆቦ የሆነባቸው ወይዘሮ እናኑ “በቀድሞው ቤቴ ያሳለፍኩትን ሳስታውሰው ዳግም እንደተወለድኩ ነው የምቆጥረው” ብለዋል፡፡
በእድሉ ተጠቃሚ የሆኑት ሌላኛዋ የቤት ባለቤት ወይዘሮ ይደመሙ ታደሰ ይባላሉ፡፡ ወይዘሮ ይደመሙ በመንገድ ፅዳት ስራ ተሰማርተው ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩ የአንድ ልጅ እናት ናቸው። “እዚህ ቤት የገባሁት ልጄ በሽተኛ ስለነበር መንግስት ሰጥቶኝ ነው።” ሲሉ በ2011 ዓ.ም ስለተሰጣቸው ቤት የሚያስታውሱት ወይዘሮ ይደመሙ፣ “አሁን እድለኞች ነን፤ ልጄም ታክሞ ድኖ ትምህርቱን እየተከታተለ ይገኛል›› ብለዋል፡፡
ወይዘሮ ይደመሙ የቤታቸውን ቁልፍ ሲረከቡ፣ “ከጭቃ ቤት ወደ ብሎኬት ቤት በመግባቴ ተደስቻለሁ” የሚሉት ወይዘሮዋ፣ የቤት እድሳት ላከናወነላቸው የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ላቅ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም በዚህ ስራ ለተሳተፉ እና ላስተባበሩ የክፍለ ከተማ እና የቀጠና ኃላፊዎችን አመስግነዋል፡፡ የ 14 ዓመት ልጃቸው ዳንኤል ንጉሴም ቤታቸው በዚህ መልኩ ተሰርቶ በማየቱ መደሰቱን ገልጿል፡፡
እድሳት የተከናወነለት ሦስተኛው ቤት ባለቤት የ94 አመቱ አዛውንት አቶ ትርፌ ተግባሩ ናቸው፡፡ አቶ ትርፌ ተግባሩ በወረዳው ማህበራዊ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው እርጅና ሳይበግራቸው ሀገራቸውን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ቤታቸው እድሳት እስኪደረግለት ድረስ ከልጆቻቸው እና የልጅ ልጆቻቸው ጋር ለረጅም ዓመታት በዚሁ ቤት ኖረዋል፡፡ በቁልፍ ርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ ቤታቸው በአዲስ መልክ በብሎኬት ተሰርቶ፣ አምሮበት እና በአስተማማኝ መልኩ ተገንብቶ፤ አሁን ላይ ያለውን ገፅታ ሲመለከቱ የተደሰቱት አዛውንቱ “ዛሬ ብሞት አይቆጨኝም፡፡ እንኳን በእውኔ በህልሜም ይህን አያለው ብዬ አስቤ አላውቅም” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ባለስልጣኑ የገነባቸው አራቱ መኖርያ ቤቶች እያንዳንዳቸው ሶስት ክፍል ሲኖራቸው ዘመናዊ መፀዳጃ ቤትም አለው፡፡ ቤቶቹ ከመሬት ከፍ ተደርገው በመገንባታቸው ከእንግዲህ ዶፍ ሲዘንብ ውሎ ሲዘንብ ቢያድር ጎርፍ ቤቴ ይገባ ይሆን ብለው ወይዘሮ እናኑ እና ጎረቤቶቻቸው አያስቡም፡፡ በተጨማሪም በዘመናዊ መልክ የተሰራው መፀዳጃ ቤት አካባቢውን ከመጥፎ ሽታ ነፃ አውጥቶታል፡፡
በርክክቡ ላይ የተገኙት የአካባቢው ነዋሪ እና የቀጠናው ኮሚቴ አቶ ደጀኔ ቶልቻ፣ ባለስልጣኑ የሰራውን ስራ በማድነቅ “ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ያከናወነው ተግባር ለሌሎች አርአያ የሚሆን ነው” በማለት ሌሎች ባለሀብቶች፣ መንግስታዊ እና የግል ተቋማት እንዲሁ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአዲስ አባባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በ2017 በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከአደሳቸው አራት ቤቶች በተጨማሪ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ቦሌ አራብሳ ሳይት 5 አንድ ቤት፣ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አማኑኤል አካባቢ አንድ እንዲሁም ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 አምስተኛ አካባቢ ሁለት ቤቶችን ገንብቶ በማጠናቀቅ ለባለቤቶቹ አስረክቧል፡፡
ባለስልጣኑ አብረውት የሚሰሩትን ተቋራጮች እና አማካሪ ድርጅቶችን በማስተባበር በበጀት ዓመቱ ለሰራቸው 8 ቤቶች 7 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጎል። የቤቶችን ዲዛይን በማውጣት እና ሂደቱን በመከታተል ግንባታው እንዲጠናቀቅ አድርጓል፡፡ የባለስልጣኑን ዓላማ በመረዳት አጋርነታቸውን ካሳዩ መካከል ይርጋለም ኮንስትራክሽን፣ ድሪባ ደፈርሻ ኮንስትራክሽን፣ ሜልኮም ኮንስትራክሽን፣ ሶፍ ኡመር ኮንስትራክሽን እና ጥላሁን ኮንስትራክሽን ይገኙበታል፡፡ ሁሌም በጎ ፈቃድ ሥራዎችን በማከናወን የሚታወቀው የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሰልጣን በ2018 በጀት ዓመት ለ30 አቅመ ደካሞች ቤቶችን ለማደስ በእቅድ የያዘ ሲሆን ከቤት እድሳት በተጨማሪ ሌሎች የበጎ ፍቃድ ስራዎችንም አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
በላዋይሽ ቢተው