ዘመናዊው የግብይት ማዕከል በ4 ኪሎ

You are currently viewing ዘመናዊው የግብይት ማዕከል በ4 ኪሎ

በእግር የመጓዝ ልምድ ካለዎት ከጥቂት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የነበሩትን የእግረኞች መንገድ ገፅታ ማስታወስዎ አይቀርም፡፡ በእነዚያ መንገዶች እንደ አሸዋ፣ ድንጋይ፣ ጠጠር እንዲሁም ሲሚንቶ ያሉ የተከመሩ የግንባታ ግብዓቶች እና ተረፈ ምርቶች፣ እንደ ሥራ ቦታ ማስፋፊያነት የሚጠቀሙ የንግድ ተቋማት፣ ሕገ ወጥ የመንገድ ዳር ንግዶች የመሳሰሉት እንቅፋት ሆነው ማስቸገራቸው ይታወሳል። ይህ ሁኔታ የእግረኛውን እንቅስቃሴ በማስተጓጎል ለትራፊክ አደጋ ጭምር ተጋላጭ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ስለመሆኑ በርካቶች ምስክር ናቸው፡፡ አዲስ አበባን የማይመጥን ገፅታ ተላብሶ የቆየው ሰዎች ማፋሰሻ ቱቦዎችን፣ አጥሮችን እንዲሁም ወንዞችን እንደመጸዳጃ እና ቆሻሻ ማስወገጃ የመጠቀሙ ጉዳይ ለእግረኛ ተጓዥ የጤና ጠንቅ እስከመሆን ደርሶ የነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ 

እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው የመዲናዋ የቀደሙ ገፅታዎቸ አሁን ላይ እጅግ በሚያስደንቅ ሁኔታ ተለውጠዋል። ለውጡን ለመታዘብ በየጎዳናዎቹ መንቀሳቀስ፣ ዓይንን ገልጦ መመልከት፣ ያለፈውን የከተማዋን ገፅታ ማስታወስ እና ሚዛናዊነት ባለው አዕምሮ ማነጻጸር በቂ ነው፡፡  እኔም፤ ከአምስት ኪሎ ወደ አራት ኪሎ የሚወስደውን መንገድ ግራና ቀኝ እያማተርኩ በተጓዝንኩበት ወቅት የተመለከትኩት የከተማዋ ዕድገት እና መሻሻል አድናቆት ፈጥሮብኛል። እንደስሟ አዲስ ሆና የተሞሸረችው አዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተሠሩ ባሉ የኮሪደር ልማት ሥራዎች እየተደመምኩ መዳረሻዬን በመሐል አራት ኪሎ ተገንብቶ በቅርቡ ለአገልግሎት በበቃው የአራት ኪሎ የገበያ ማዕከል አደረግሁ፡፡

በመዳረሻዬ የተመለከትኩት ለውጥ በጣም የሚያስደንቅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ከዚህ ቀደም ይህ አካባቢ በጠባቡ የእግረኛ መንገድ ላይ የጎዳና ንግድ ታክሎበት የእግረኛውን የመንቀሳቀስ መብት ያስተጓጉል ነበር፡፡ አሁን ባለው ገጽታ አይደለም ለእግረኛ ቀርቶ ለባለ ሁለት እግር ተሽከርካሪ (ሳይክል) መንጃ ምቹ የሆነ መንገድ እንዲሁም በሰፋፊ የእግረኛ መንገድ ላይ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቢደክሞት እንኳን አረፍ የሚሉበትና ጋዜጣ የማንበብ ፍላጎትዎን የሚያረካ ስፍራ ተዘጋጅቷል፡፡ በተለይ ወደ አራት ኪሎ የገበያ ማዕከል ጎራ ሲሉ ለመኪናዎ ደህንነትዎ ምቹ የሆነ የማቆሚያ ስፍራ ተዘጋጅቷል፡፡

የአራት ኪሎ የገበያ ማዕከል የነዋሪውን ኢኮኖሚያዊ ብሎም ማህበራዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ሚናው የላቀ መሆኑን የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው በማዕከሉ ምርትና አገልግሎት ለመሸጥ የገቡ ነጋዴዎች እንዲሁም ግብይት የሚፈፅሙ ነዋሪዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል፡- በኪዊንስ ሱፐር ማርኬት ብርቱካን፣ አቮካዶ… ሲሸምቱ ያገኘናቸው አቶ ብሩክ ቡልቻ አንዱ ናቸው፡፡ ለምን ይህንን ሱፐር ማርኬት እንደመረጡ ላቀረብንላቸው ጥያቄ፤ የኪዊንስ ሱፐር ማርኬት ከዚህ ቀደም ማዕከሉን ፒያሳ አድርጎ ምርቶቹን በሚሸጥበት ጊዜ የረጅም ጊዜ ደንበኛ መሆናቸውን በማስታወስ፤ ሱፐር ማርኬቱ በምርቶቹ ጥራት እና በዋጋ ተመጣጣኝነቱ በሸማቹ ሕብረተሰብ የሚመረጥ ነው፡፡ የእሳቸውም አመጣጥ ያ ጥሩ ስምና ዝና ያለው የንግድ ተቋም አዲስ በተከፈተው የአራት ኪሎ የገበያ ማዕከል ሥራ መጀመሩን በመስማታቸው እንደሆነ ገልፀውልናል፡፡  

እንደ አቶ ብሩክ ገለፃ፤ ወደኪዊንስ ሱፐር ማርኬት ከመጡ ከሚገዟቸው ምርቶች አንዱ ብርቱካን ነው፡፡ እኛም በተገኘንበት ዕለት አንዱን ኪሎ ብርቱካን በ109 ብር፣ አቮካዶም እንዲሁ በ54 ብር ገዝተዋል፡፡ እነዚህን ምርቶች አካባቢያቸው ላይ ካለ የፍራፍሬ መሸጫ ሱቅ የሚገዙት ብርቱካን በ200 ብር እና አቮካዶ በ58 ብር ነው፡፡ አራት ኪሎ ይህንን የመሰለ የገበያ ማዕከል መገንባቱ በአካባቢው እንቅስቃሴ ለሚያደርግ ሰው ጥሩ የገበያ አማራጭ የፈጠረ ነው፡፡

ለመኪናቸው ደህንነት ምንም ሳይጨነቁ ተረጋግተው በሌሎች ሱቆች የሚፈልጓቸውን ነገሮች ከሸመቱ በኋላ ትንሽ አረፍ ብለው፤ ሻይ ቡና በማለት ለራሳቸው ጥሩ ጊዜ እንዳገኙ የሚናገሩት አቶ ብሩክ፣ አብዛኛውን ጊዜ በሥራ ተወጥረው እንደሚያሳልፉ፣ በሥራ አካባቢያቸው ሁሉንም እቃ በአንድ ቦታ መሸመት የሚያስችል እንዲህ አይነት የገበያ ማዕከል እንደሌለ እንዲሁም ጊዜን ብሎም ጉልበትን እንደሚቆጥብ መስክረዋል፡፡ በማዕከሉ የቀረቡ ምርቶች ከዋጋ አንፃር ተመጣጣኝ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡ 

በማዕከሉ የኪዊንስ ሱፐር ማርኬት ስራ አስኪያጅ አቶ መኪ ዲጋ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ማብራሪያ፤ በምግብ የፍጆታ እቃዎች ላይ ተገቢውን ቅናሽ በማድረግ የነዋሪውን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ምርቶች ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አስራ ሁለተኛ ቅርንጫፍ በሆነው የአራት ኪሎ የገበያ ማዕከል ውስጥ የሚገኘው ኪዊንስ ሱፐር ማርኬት ከሚድሮክ እህት ኩባንያዎች ከሆነው የእርሻ ልማት የሚገኙ ምርቶች ላይ ቅናሽ በማድረግ ለተጠቃሚዎች እየተሸጠ ይገኛል፡፡ በቅናሽ ዋጋ የሚያቀርቧቸው የአግሮ ኢንዱስትሪ ምርቶች እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ውጤቶች በስፋት በሸማቾች ዘንድ ተፈላጊ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከዋጋ አንፃር ተመጣጣኝ ብሎም የሸማቹን ኪስ የማይጎዳ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የሚድሮክ እርሻ ልማት ውጤት የሆኑት የፍራፍሬ ምርቶች እንደ ብርቱካን፣ አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ካሮት የመሳሰሉ  እንደቅደም ተከተላቸው በኪሎ ግራም በ109፣ በ54፣ በ40 እና በ72 ብር ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ተችሏል፡፡ በአራት ኪሎ የገበያ ማዕከል ውስጥ ይህን መሰል አገልግሎት መስጠት መቻላቸው የከተማዋን ነዋሪ በቅርበት ለመድረስ እንደሚያስችላቸውም አብራርተዋል፡፡

በገበያ ማዕከሉ ያደረግነው ቅኝት አላበቃም፡፡ ሌላኛው መዳረሻችንን ያደረግነው በፀሃይ ኮስሞቲክስ ሱቅ ነው። በዚህ ሱቅ የተለያዩ ዘመናዊ ልብሶች፣ የመዋቢያ እቃዎች እንዲሁም ቦርሳዎችን ሲሸጡ ያገኘናቸውን ወይዘሮ እፀገነት አስፋው አነጋግረናል፡፡ የቀድሞዋ አራት ኪሎ አሁን ላይ ተውባ እና የዘመኑ የአሰራር ሂደቶችን ተከትላ መታደሷ ወደ አካባቢው ለሚመጣ ሠው ጥሩ ቆይታ የሚያደርግበትን ገፅታ እና ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን መስክረዋል፡፡ ወደ አካባቢው የመጡና ወደ ግብይት ማዕከሉ ጎራ ያሉ እንደየ ፍላጎታቸው ሸምተው መሄድ የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ጥሩ የሆነ የመኪና ማቆሚያ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱ ተሽከርካሪ ይዞ የሚመጣ ሠው ያለአንዳች መቸገር የሚፈልገውን ግብይት ጊዜ ወስዶ መፈፀም የሚችልበት ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ እፀገነት ገለፃ፤ በሱቃቸው ከ600 ብር እስከ 2 ሺህ ብር የሚያወጡ የተለያዩ ዘመናዊ አልባሳት አሏቸው፡፡ የመዋቢያ ቁሳቁሶች እንደ የጆሮ ጌጥ፣ ፀጉር ማስያዣ የመሳሰሉት እንዲሁ ከ200 ብር አንስቶ እስከ 500 ብር ድረስ ይሸጣሉ። የገበያ ማዕከሉ ከየትኛውም አቅጣጫ ለሚመጣ ሸማች ለትራንስፖርት ምቹ በሆነ ስፍራ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

“የአራት ኪሎ የገበያ ማዕከል ሥራ መጀመሩን ከጓደኞቼ ጋር በእግር ጉዞ በምናድግበት ወቅት ነው ያወቅነው” የምትለው ወጣት ሃና፤ በማዕከሉ ተንቀሳቅሳ የሱቆቹን የምርት ዓይነት በመመልከት አድንቃ ብቻ አልተመለሰችም፡፡ የሚያስፈልጓትን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ በማግኘቷ ጊዜ ሳታጠፋ ገዝታለች፡፡ ይህንን አስመልክቶ እንደገለፀችልን፤ ልብስ በ1 ሺህ 200 ብር፣ ጫማ በ1 ሺህ 500 ብር፣ የፀጉር ቅባት በ300 ብር እንዲሁም ሻምፖዎችን በ500 ብር ገዝታለች፡፡ ይህም ከዚህ ቀደም በሌሎች ሱቆች ትገዛው ከነበረው አንፃር በዋጋ ቅናሽ ያለው መሆኑን አብራርታለች፡፡ 

ሌሎችም ጥሩ ለአይን ማረፊያ የሆኑ ባህላዊ ቁሳቁሶች መሸጫ መኖሩን መታዘቧን የምትናገረው ወጣት ሃና የተለያዩ ትኩስ ፍራፍሬዎችንም በዚሁ የገበያ ማዕከል ማግኘት መቻሏን አክላለች፡፡

በቅርቡ የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የ4 ኪሎ የገበያ ማዕከልን፣ መኪና ማቆሚያን እና 4 ኪሎ ፕላዛን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ማድረጋቸው ይታወሳል። ፕሮጀክቶቹ ከመሬት በታች የተገነቡ እጅግ ዘመናዊ 102 የስጦታ እና የአልባሳት መደብሮች፣ ካፍቴሪያዎች፣ ማንበቢያ ስፍራዎች፣ ሱፐር ማርኬቶች፣ ከ100 በላይ ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ የሚያስተናግድ የመኪና ማቆሚያ እና  በአንድ ጊዜ እስከ 5 ሺህ ሰዎችን መሰብሰብ የሚያስችል የፕላዛ፣ የአንፊ ቴአትርና የተለያዩ የጥበብ ስራዎችን ማቅረቢያ ስፍራዎችን መያዛቸውን፤ የሲቪል ተሳትፎን፣ የባህል ዕድገትን፣ የእግር ጉዞን የሚያበረታቱ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ፣ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በተለይም አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ከንቲባዋ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ያጋሩት መረጃ ያመላክታል።

አዲስ ልሳን ጋዜጣ በሐምሌ 26 ዕትሟ የ4 ኪሎ ፈርጦች በሚር ርዕስ ባስነበበችው ጽሑፍ ላይ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚክ አሶሴሽን ከፍተኛ ተመራማሪ ሞላ አለማየሁ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣  አንዲት ከተማ ምቹ ለመባል መሰረታዊ የሆኑ አገልግሎቶችን ማሟላት አለባት። ከዚህ በተጨማሪም ነዋሪዎች የተሻለ የሚዝናኑበትን መሰረተ ልማት ማሟላት ይኖርባታል፡፡ በአጠቃላይ ዜጎች የሚፈልጉትን መሰረተ ልማት በበቂ ሁኔታና በጥራት ማቅረብ የምትችል ከተማ ለኑሮ ምቹ ነች ተብሎ ይታሰባል፡፡

የአንድ መስኮት አገልግሎት የሚባሉ አሰራሮች በመላው አለም እየተለመዱ መጥተዋል የሚሉት ሞላ (ዶ/ር)፣ የአራት ኪሎ ፕሮጀክቶች ንግድ ያቀላጥፋሉ፤ ጊዜን ይቆጥባሉ፤ የስራ እድል ይፈጥራሉ፤ ሻጭና ገዥን በአንድ ያገናኛሉ፣ የኑሮ ደረጃን ያሻሽላሉ፤ ምክንያቱም ብዙ አገልግሎቶችን በአንድ የያዘ ማእከል ነው፡፡ ስለዚህ ከተማዋን ምቹ ከማድረግ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውም ከፍተኛ ነውና ወደ ሌሎች ቦታዎች መስፋፋት እንዳለባቸው አብራርተዋል፡፡

በሄለን ጥላሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review