የሊጉ ጅማሮና ተጠባቂ ጨዋታዎች

You are currently viewing የሊጉ ጅማሮና ተጠባቂ ጨዋታዎች

እንደ ጎል ዶት ኮም መረጃ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እስከ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን የሚደርስ የቴሌቪዥን ተመልካች ያለው ተወዳጅ ውድድር ነው፡፡ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውና የዓለማችን ምርጥ ተጫዋቾችና አሰልጣኞች የሚፋለሙበት ይህ ውድድር በትላንትናው ዕለት ተጀምሯል። የተጫዋቾች ዝውውር መስኮት ተሳትፎ፣ የቅድመ ውድድር ጊዜ የወዳጅነት ጨዋታዎች እና የአዳዲስ ታክቲኮች ሙከራ ደግሞ የሊጉ ክለቦች የዝግጅት ምዕራፍ ዋና ዋና ጉዳዮች ነበሩ።

ክለቦች ለቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅት በዋናነት በአሜሪካ እና በእስያ የሚገኙ ሀገራትን ጎብኝተዋል። በዚህ ጉዞ ወቅት ከሌሎች ታላላቅ የአውሮፓ ክለቦች ጋር የወዳጅነት ጨዋታዎችን በማድረግ አዳዲስ ተጫዋቾችን እና ስልቶችን ሞክረዋል። በውድድርና እረፍት ላይ ሆነው ቀጣዩን የውድድር ዘመን ለማሳመር ድክመታቸውን ማረሚያ መላ ሲፈለጉ ከርመዋል፡፡ እንደዚሁም ባለፈው ዓመት ባስመዘገቡት ውጤት ላይ ተመስርተው አብዛኞቹ ክለቦች በዝውውር ገበያው ላይ ትልቅ ኢንቨስትመንት አድርገዋል። በዚህም ክለቦች የጎደሉባቸውን ቦታዎች በአዳዲስ ተጫዋቾች ለመሙላት እና የተዳከሙ ክፍሎችን ለማጠናከር ጥረት አድርገዋል።

የዓለማችን ባለ ብዙ ተመልካቹ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመን እንደ አርሰናል እና ማንቼስተር ዩናይትድ ያሉ ክለቦች የአዲሱ ውድድር ዘመን ጅማሬያቸው ከግዙፍ ተጋጣሚዎች ጋር አገናኝቶ የውድድሩን ሂደት ገና ከወዲሁ አጓጊ አድርጎታል፡፡ ሻምፒዮን እንዲሆን በተጠበቀበት ያለፈው የውድድር ዘመን ለሦስተኛ ተከታታይ ዓመት በሊጉ 2ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የሚኬል አርቴታው አርሰናል አዲሱን የውድድር ዘመን ወደ ኦልድትራፎርድ በመጓዝ ይጀምራል።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከፍተኛ ተሳትፎ ያደረገው ክለቡ እንደ ትራንስፈር ማርኬት መረጃ እስካሁን ድረስ ለስድስት ተጫዋቾች ግዢ ከ200 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ወጪ አድርጓል፡፡ የ13 ጊዜ የሊግ አሸናፊው አርሰናል የመጀመሪያ ጨዋታውን ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር የሚያደርግ ሲሆን፣ በውድድር ዓመቱ በሜዳው የመጀመሪያው ጨዋታ በኤምሬትስ ስታዲየም አዲስ አዳጊውን ሊድስ ዩናይትድ ያስተናግዳል፡፡ ለሶስተኛው ሳምንት መርሃ ግብር ወደ አንፊልድ ተጉዞ ከሻምፒዮኑ ሊቨርፑል ጋር ትልቁን ጨዋታ ያከናውናል፡፡

በ4ኛ እና 5ኛ ሳምንት ኖቲንግሃም ፎረስት እና ማንችስተር ሲቲ የሚኬል አርቴታን ከዋንጫ ማምጣት ግዴታ ጋር የሚጀምር ውድድር ዘመን ሊያከብዱ የተሰለፉ ሌሎች ክለቦች ናቸው።

የአርሰናል እግር ኳስ ክለብ ባለፉት ሶስት የውድድር ዘመናት በተከታታይ የፕሪሚየር ሊጉን ሁለተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቅቋል። ቡድኑ በዝውውር መስኮት ላይ ቪክቶር ጂዮኬሬሽን በመሳሰሉ ተጫዋቾች በመጠናከሩ ብዙ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ፣ አርሰናል ለዋንጫው አሸናፊነት ከፍተኛ ግምት አግኝቷል፡፡

የ2024/25 የውድድር ዘመን በክለቡ የፕሪሚየር ሊግ ተሳትፎ ታሪክ እጅግ አስከፊው ነበርና ለቀጣዩ ተጠናክሮ መቅረብ የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪምና የክለቡ ኃላፊዎች ቀዳሚ ተግባር ነው። ብራዚላዊውን ማቲውስ ኩንሃን ከወልቭስ፣ ምቡሞን ከብራይተን እንደዚሁም ግዙፉን አጥቂ ቤንያሚን ሼሽኮ ከወደ ጀርመን አስመጥቷል፡፡ ሌሎች ዝውውሮችን ለመጨረስ የሂሳብ መዝገቡን ማስተካከያ መላ እየፈለገ ያለው ዩናይትድ በኦልድትራፎርድ አርሰናልን በማስተናገድ የውድድር ዘመኑን የሚከፍት ሲሆን፣ ከዚያም ወደ ክራቨን ኮቴጅ አቅንቶ ፉልሃምን ከገጠመ በኋላ በሜዳው በርንሌይን ይጋብዛል፡፡

በማንችስተር ደርቢ ወደ ኢቲሃድ በማቅናት ማንችስተር ሲቲን ከሚገጥምበት የ4ኛ ሳምንት መርሃ ግብር መልስ በሜዳው ከቼልሲ ጋር የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች የሩበን አሞሪምን ጅምር ከሌሎቹ ክለቦች አንጻር ከባድ እንዲመስል ያደርጉታል።

ከሻምፒዮንነት ደስታቸው መልስ አስደናቂ ዝውውሮችን እየፈፀሙ በሌላ ከፍታ እየመጡ ያሉት ቀዮቹ ሊቨርፑሎች ሚሎሽ ኬርኬዝን ከወስዱበት ቦርን ማውዝ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ አዲሱን የውድድር ዘመን እንደሚከፍቱ የሊጉ መርሃ ግብር መረጃ ያሳያል፡፡ ኒውካስል ዩናይትድ የመርሲሳይዱ ክለብ የውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ እውነተኛ ፈተና ሊሆን 2ኛ ሳምንት ላይ በሜዳው ይጠብቃቸዋል፡፡ በሦስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ያለፈው የውድድር ዘመን ተከታያቸው አርሰናልን የሚገጥሙበት ጨዋታ የአርነስሎትን ቡድን መልክ የማሳየት አቅም አለው። በ4ኛ ሳምንት በአንፃራዊነት ቀለል ባለው መርሃ ግብር ከበርንሌይ ጋር ከተጫወተ በኋላ በመርሲሳይድ ደርቢ ብርቱ ፉክክር የሚደረግበትን ጨዋታ ከሜዳው ውጭ ያደርጋል ይላል ቢቢሲ ያጋራው መረጃ፡፡

የሊቨርፑል እግር ኳስ ክለብ ባለፈው የውድድር ዘመን በአርነስሎት አመራር ስር የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት ችሏል። ቡድኑ ጥቂት ወሳኝ ተጫዋቾችን ቢሸጥም፣ በዝውውር ገበያ ላይ ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት እንደ ፍሎሪያን ዊርትዝ እና ሌሎችም ኮከብ ተጫዋቾችን አስፈርሟል። ይህ ደግሞ ይበልጥ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚያደርገውና በዚህም ምክንያት የዘንድሮው የዋንጫ ለአሸናፊነት የተሰጠው ግምት ከፍተኛ ሆኗል።

ከውጤት አንፃር ዥንጉርጉር መልክ ካለው የውድድር ዘመን በኋላ በዝውውር መስኮቱ በንቃት በመሳተፍ ራሱን እያጠናከረ ያለው ማንቸስተር ሲቲ የ2025/26 ተጋጣሚዎቹን ያወቀው በዓለም ክለቦች ዋንጫ ተሳትፎ ላይ ሆኖ ነው። ያለ በቂ እረፍትና ዝግጅት በአዲሱ የውድድር ዘመን በመክፈቻው መርሃ ግብር ወልቭስን የሚገጥም ሲሆን ቶተንሃም፣ ብራይተን፣ ማንችስተር ዩናይትድ እና አርሰናል በመጀመሪያዎቹ አምስት ሳምንታት የሚገጥማቸው ቡድኖች ናቸው።

ሎስ አንጀለስ ኤፍሲን በማሸነፍ የዓለም ክለቦች ዋንጫ ጅምሩን ያሳመረው የኤንዞማሬስካው ቡድን ቸልሲ ከአሜሪካ ሲመለስ ወደ ሊግ ሻምፒዮንነት መንበር የመጠጋት ዓላማ እንደሚኖረው ይጠበቃል። በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ከአራት የለንደን ክለቦች ጋር በመጫወት የ2025/26 ውድድር ዘመንን የሚጀምሩት ሰማያዊዎቹ፣ በግዝፈት ምድብ እኩዮቻቸው ከሆኑት ክለቦች አንጻር ቀለል ያሉ ተጋጣሚዎች ያገኙ ይመስላሉ።

ከክሪስታል ፓላስ፣ ዌስትሃም ዩናይትድ፣ ፉል ሃም እና ብሬንት ፎርድ ጋር የሚጫወተው ቼልሲ አምስተኛው ሳምንት ላይ ከሜዳው ውጭ ማንችስተር ዩናይትድን ይገጥማል። በተለይም በዓለም የክለቦች ዋንጫ ምክንያት በቂ የማገገሚያ እረፍት አለማግኘታቸው የምዕራብ ለንደኑ ክለብና የጣልያናዊው አሰልጣኝ ፈተና ይመስላል።

በፈረንሳዊው አሰልጣኝ ሬጂስ ለብሪስ እየተመራ ሰንደርላንድ ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የተመለሰው ሊድስ ዩናይትድ፣ በርንሌይ እና ሰንደርላንድ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማደጋቸው ይታወቃል። ኢፕስዊችታውን፣ ሌይስተር ሲቲ እና ሳውዝሃምፕተን በተቃራኒው ከእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ወደ ሻምፒዮንሺፕ የወረዱ ክለቦች ናቸው።

የሊጉ አዳዲስ ህጎች

የ2025/26 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመን የጨዋታውን ፍጥነት እና ፍትሃዊነት ለማሻሻል ታስበው የመጡ አዳዲስ ህጎች አሉ። እነዚህ ህጎች በተለይም የግብ ጠባቂዎችን ባህሪ፣ የተጫዋቾችን ከዳኞች ጋር የሚያደርጉትን ግንኙነት እና የቫር ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ይመለከታሉ።

የጨዋታ ጊዜን ማባከን ለመከላከል የግብ ጠባቂዎች ኳሱን በእጃቸው መያዝ የሚችሉበት ጊዜ ከስድስት ወደ ስምንት ሰከንዶች ከፍ ብሏል። ይህ ህግ ቀድሞም የነበረ ቢሆንም ብዙ ጊዜ ተግባራዊ አይደረግም ነበር። አሁን ግን ዳኞች ከ5 ሰከንድ ጀምሮ በጣት ምልክት ጊዜውን ያሳያሉ፤ ከስምንት ሰከንድ በላይ የያዘ ግብ ጠባቂ ቡድኑ ላይ የማዕዘን ምት (corner kick) እንዲሰጥበት ያደርጋል አዲሱ ህግ።

በሌላም በኩል ጨዋታ ላይ ብዙ ተጫዋቾች ዳኛን ከብበው ሲከራከሩ የሚታየውን ሁኔታ ለመቀነስ፣ አሁን ላይ ከዳኛው ጋር ስለ ውሳኔዎች መወያየት የሚችለው የቡድኑ አምበል ብቻ እንደሆነና ከሱ ውጪ ያለ ተጫዋች ሳይፈቀድለት ወደ ዳኛው ከቀረበ ቢጫ ካርድ ሊሰጠው እንደሚችል ተደንግጓል።

ከፊል- አውቶማቲክ የጥፋት  (Offside) ቴክኖሎጂ ባለፈው የውድድር ዘመን መጨረሻ ላይ መተግበር የጀመረ ሲሆን፣ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ሙሉ በሙሉ አገልግሎት ላይ ይውላል ተብሏል። ይህም የጥፋት ውሳኔዎችን በፍጥነትና በትክክል ለመወሰን እንደሚረዳና የቫር ውሳኔዎች ላይ የሚፈጠረውን መዘግየት እና ውዝግብም እንደሚቀንስ ይጠበቃል። እንደዚሁም ውሳኔዎችን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ይረዳ ዘንድ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ዳኞች የቫር ውሳኔዎችን ከገመገሙ በኋላ፣ ውሳኔውን በስታዲየሙ ድምፅ ማጉያ (public address system) አማካኝነት ለደጋፊዎች እንዲያብራሩ ይፈቀድላቸዋል።

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አወዳዳሪው አካል ይፋ ያደረገው ሌላኛው ህግ የፍጹም ቅጣት ምትን የተመለከተ ሲሆን አንድ የፔናሊቲ ምት የሚመታ ተጫዋች ኳሷን ድንገት ሁለት ጊዜ ቢነካት፣ ቀድሞ የነበረው ቅጣት ተሰርዞ ፔናሊቲው እንደገና እንዲመታ ይደረጋል። ይህም ባልታሰበ ስህተት ምክንያት የቡድኑን ጥቅም እንዳይቀንስ ይረዳል ተብሎ ታምኖበታል። እነዚህ አዲስ የሚተገበሩ ህጎችም በጨዋታው ላይ ትልቅ ተጽእኖ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review