በወጣቶች ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የሽኖዬና የጎቤ በዓል የቆየ ባህላዊ ቱውፊቱን ጠብቆ መከበር እንዳለበት የኦሮሞ አባገዳ ህብረት ገልጿል፡፡
በዓሉ ከነሃሴ ወር መጨረሻ ጀምሮ እስከ መስቀል በዓል እንደሚከበርም ህብረቱ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች የበርካታ ባህላዊ ቱውፊቶች ባለቤቶች መሆናቸውን ያስታወቁት የቱለማ ኦሮሞ አባገዳና የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ጸሓፊ አባገዳ ጎበና ሆላ፣ ከእነዚህም መካከል አንዱ በኦሮሞ ወጣቶች ዘንድ በጫዋታ የሚከበረው የሽኖዬና ጎቤ በዓል፣ የአሮጌ ዓመት መሸኛና የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ ተደርጎ ወጣቶች በአባቶችና ተላላቆቻቸው የሚመረቁበት ነው ብለዋል፡፡
በዓሉ ከነሃሴ ወር መጨረሻ ጀምሮ እስከ መስቀል በዓል ድረስ እንደሚከበር የገለጹት አባገዳ ጎበና ሆላ፣ በዓሉም ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ከ12 እስከ 25 አመት ያላቸው ታዳጊ ወጣት ወንዶችና ሴቶች እንደሚሳተፉበት ተናግረዋል፡፡
የሽኖዬና ጎቤ በዓል ባህላዊ ወግና እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር የወጣቱ ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት አባገዳ ጎበና ሆላ፣ ወጣቶች ጫወታ በሚያከብሩበት ወቅትም ካልተገቡ ነገሮች በተጠበቀ መልኩ ማክበር እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
በዓለሙ ኢላላ